የሎጀስቲክስ ስትራቴጂ መተግበር የዘርፉን ችግሮች በመፍታት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው

66

አዲስ አበባ ነሀሴ 10/2012 (ኢዜአ) የብሔራዊ ሎጀስቲክስ ስትራቴጂ መተግበር በአሰራር ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን የማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን ገለጸ።

የኢትዮጵያ የወደብ አገልግሎት ዘርፉ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክትና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢም የሚያስገኝ መሆኑ ይታወቃል።

ከዘርፉ ጠቀሜታ አንፃር የሎጀስቲክስ ስርአቱን መስመር ለማስያዝና አገሪቱን ተጠቃሚ ለማድረግ በአገር አቀፍ ደረጃ የ10 ዓመት ብሔራዊ ሎጅስቲክስ ስትራቴጂ ሲዘጋጅ መቆየቱም የሚታወስ ነው።

ስትራቴጂ ከባለፈው አመት ጀምሮ እየተተገበረ ሲሆን በተለይ በሎጅስቲክስ ስርአቱ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ የማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን ገልጿል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በሎጀስቲክስ ላይ ያሉ መሰረተ ልማቶች ከአገሪቱ የገቢና ወጪ እድገት ጋር የሚመጣጠን አይደለም።

እቃዎችን በፍጥነት በማስገባትና በማስወጣት ረገድም ውስብስብና አመቺ ያልሆኑ አሰራሮች እንደነበሩ ያነሳሉ።

በዚህም እቃዎችን በማጓጓዝ ሂደት ላይ ቀልጣፋ አሰራር ባለመኖሩ የሚፈልገው ወጪም ከፍተኛ መሆኑን ይገልጻሉ። 

በተለያዩ ጊዜያት ወደ አገር ውሰጥ የሚገቡና የሚወጡ የወደብ እቃዎች እየጨመሩ ቢሆንም የወደብ የማስተናገድ አቅም ግን ውስን መሆኑን አቶ መኮንን ይገልፃሉ።

ከመርከብ የሚራገፉ እቃዎችን በአፋጣኝ ለማንሳት የአቅም ውስንነት መኖርም ሌላኛው ችግር መሆኑን ይናገራሉ።

አሁን ያለው የመንገድ መሰረተ ልማት፣ ባቡርና መኪና እያደገ ከመጣው የገቢና ወጪ የወደብ እቃዎች ጋር ሲነፃፀር የሚመጣጠን አለመሆኑንም ገልጸዋል።
በመሆኑም ለችግሮቹ መፍትሄ ያስቀምጣል የተባለው ብሔራዊ የሎጅስቲክስ ስትራቴጂ ባለፈው አመት በይፋ መተግበር መጀመሩ ይታወቃል።

ተግባራዊ መደረጉ በዘርፉ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በአገሪቱ በኮንቴነር ታሽጎ ወደ ውጭ የሚላክ እቃ 7 በመቶ ብቻ ነበር።

እንደ አቶ መኮንን ገለፃ በ2011 እና 2012 ዓ.ም ግን 52 በመቶ እቃ በአገር ውስጥ በማሸግ መላክ ተችሏል።

የብሔራዊ ሎጅስቲክስ ስትራቴጂ ተግባራዊ መደረጉ ደግሞ ይበልጥ ውጤታማ እያደረገው መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም የብሄራዊ የሎጅስቲስ ካውንስል እንዲሁም የሎጅስቲክስ ትራንስፎርሜሽን ቢሮ የተቋቋመ ሲሆን ይህም ለዘርፉ እድገትና ውጤታማነት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

የ10 ዓመቱ የብሔራዊ ሎጀስቲክስ ስትራቴጂ ዝግጅት ላይ የዘርፉ ተዋናዮችና ባለሙያዎች ተሳትፈውበት ሲዘጋጅ 4 ዓመታትን ፈጅቷል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም