ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የለውጥ ሥራዎች ቀጣይነት እንሰራለን - የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት

123
ባህርዳር ሀምሌ 5/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የጀመሯቸው የለውጥ ሥራዎች የህዝቡን የረጅም ጊዜ ፍላጎት መሰረት ያደረጉ በመሆናቸው ለቀጣይነታቸው ጠንክረው እንደሚሰሩ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት ተናገሩ። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የምክር ቤት አባላት እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአገር ውስጥ አልፎ የሌሎች አገራትን ቀልብ መግዛት የሚያስችል ሥራ ሰርተዋል። ለእዚህም ዶክተር አብይ አህመድ ህገ-መንግስቱን በትክክለኛው መንግድ መተግበራቸውና የህዝብን ፍላጎት መሰረት አድርገው በመስራታቸው መሆኑን የምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል። ከምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ አዘነግ ደመላሽ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዝቡ ሲፈልገውና ሲናፍቀው የነበረውን ህገ-መንግስቱን መሰረት ያደረገ ሥራ በመስራታቸው ቀድሞ ለተቃውሞ ሲወጣ የነበረን ወጣት ሳይቀር ለድጋፍ እንዲወጣ ማድረግ ችለዋል። በተለይም ከህገ-መንግስቱ ውጪ በታራሚዎች ላይ ሲደርሱ የነበሩ የሰባዊ መብት ጥሰቶችን በማስቆምና የሰባዊ መብት ጥሰት ሰለባ የሆኑ የፖለቲካ እስረኞች በመፍታት በአገራዊ ጉዳይ ላይ በጋራ እንዲሰለፉ ማድረጋቸው ትክክለኛና ለአገራዊ አንድነት ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል። እንደ ወይዘሮ አዘነግ ገለጻ ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ሥራዎች ለውጦች የተመዘገቡ ቢሆንም ህዝቡን ያላሳተፈና የህዝቡን ፍላጎት ያማከለ ባለመሆኑ ወጣቱ መንግስትን እንደጠላት ሲያይ ቆይቷል። "በአሁኑ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገውንና ህገ-መንግስቱን የተከተለ ሥራ መስራት በመጀመራቸው በመቶ ቀናት ውስጥ እስከዛሬ ከተመዘገቡት ውጤቶች በበለጠ ህዝቡን ማስደሰት ችለዋል" ብለዋል። እንደ ወይዘሮ አዘነግ ገለጻ በአሁኑ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስተሩ የህዝቡን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ተግባር ያላሰደሰታቸው አካላት አሉታዊ ሀሳባቸውን ሲሰነዝሩ ይስተዋላል። "ይህንን ደግሞ ሕብረተሰቡን ወክለን  በምክር ቤት የተቀመጥን አባላት ከህዝቡ ጋራ መዋጋት ይጠበቅብናል፤  የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ከዝህቡ ጋር ሆነን እንረባረባለን” ብለዋል። "ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተወሰኑ ጊዜያት ኢትዮጵያዊያንን በፍቅር ያስተሳሰሩና ከ20 ዓመታት በላይ ተለያይተው የቆዩ የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦችን ሳይቀር አንድ ማድረግ የቻሉት ህዝባዊ መሰረት ሰላላቸው ነው" ያሉት ደግሞ አቶ እንድሪስ የሱፍ ናቸው። በውጪም ሆነ በአገር ውስጥ የሚኖሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራቸው ጉዳይ በአንድ መድረክ በያገባኛል ስሜት ተነሳስተው ወደሰላም እንዲመጡ ያደረጉ መሪ መሆናቸውን ተናግረዋል። "ወደስልጣን ከመጡ ወዲህ በተለያዩ አገራት ሳይቀር በመሄድ የታሰሩ ኢትዮጵያዊያን እያስፈቱ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማድረጋቸው ለዜጋ የሚሰጡትን ክብር ከፍ ያለ ስለመሆኑ ማሳያ ነው" ሲሉም አቶ እንድሪስ ተናግረዋል። የምክር ቤት አባላት ህዝብን ወክለው የተመረጡ እንደመሆናቸው መጠን እየተመዘገበ ያለውን ለውጥ ለማስቀጠል ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው የተናገሩት ደግሞ አቶ ላቀ ጥላየ ናቸው። ለውጡ በየደረጃው ያሉ የምክር ቤት አባላት ሲመኙት የነበረና አሁን ወደተግባር የወረደ በመሆኑ ሳይደናቀፍ እንዲቀጥል  ከሕብረተሰቡ ጋር በመሆን በትኩረት እንደሚሰሩም ተናግረዋል። ለውጡ የመላ ኢትዮጵያዊያን ስለሆነ ሕብረተሰቡ ለውጡን ለማስቀጠል በንቃት መሳተፍ እንዳለበትም አስገንዝበዋል። አሁን የታዩት ለውጦች አገሪቱን ወደተሻለ የዕድገት ደረጃ የሚያደርስ በመሆኑ የተጀመረው ህዝባዊ ድጋፍና ለውጥ እንዳይቀለበስ እያንዳንዱ ዜጋ የለውጡ አካል ሆኖ መንቀሳቀስ እንዳለበት አመልክተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም