የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት ስራን በጊዜና በጥራት ለማጠናቀቅ ማስተማሪያ ነው...የነቀምቴና የነጌሌ ከተሞች ነዋሪዎች

68

ነቀምቴ፣ነጌሌ፣ ነሐሴ 09/2012 (ኢዜአ) የሸገርን ማስዋብ የግንባታ ፕሮጀክት ባማረ መልኩ በአጭር ጊዜ መከናወን ጠንክሮ በመስራት የሃገርን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት የሚያስችል ማሳያ ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የነቀምቴና የነጌሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ በመገናኛ ብዙሃን ሲተላለፍ ባዩት የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት አፈጻጸም አድናቆታቸውን ተናግረዋል ።

የነቀምቴ ከተማ 09 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ዶክተር ሞሲሳ በሰጡት አስተያየት በአገሪቱ ያለፉት የመንግሥታት ታሪክ ውስጥ ቤተ-መንግሥትን በማስዋብና ህዝብ ገብቶ መመልከት ቀርቶ በዙሪያው ለማለፍ እንኳን ከፍተኛ ሥጋት ነበረ።

በአሁኑ ጊዜ ግን ግቢውን በማስዋብ የሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ገብተው እንደፈለጉት መዝናናት የቻሉበት ሆኖ መገኘቱ እጅግ የሚያስደስት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የከተማው 03 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሙሉጌታ ቢራቱ በበኩላቸው “የፕሮጀክቶቹ ውበት የአገሪቱን ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሚገልጽና አቃፊነትን በሚያሳይ መልኩ መዋባቸው የሚያረካ ፕሮጀክት ነው” ብለዋል።

ያለፉት የሀገሪቱ መንግሥታት ሲጠቀሙበት የነበረውን የተለያዩ ቅርሶችን በማስቀመጥና ብርቅዬ የዱር እንስሳትን በመንከባከብ ለመጪው ትውልድ ለዕይታ እንዲበቁ ማድረግ በራሱ ትልቅ ቦታ ያለው መሆኑን አስረድተዋል።

"የእንጦጦ ፓርክን የተፈጥሮ አቀማመጡ ሳይለወጥ በዚህ መልኩ ተሰርቶ ለሕዝቡ የመዝናኛ አገልግሎት መዘጋጀቱም በተለይም ወጣቱ ትውልድ እንዲማርበት የሚያደርግ ነው" ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ ኤቢሣ ጉያሣ ናቸው ፡፡

የግንባታ ፕሮጀክቶች በዚህ መልኩ በተያዘላቸው ጊዜ ጥራታቸውን ጠብቀው ሊጠናቀቁ የሚችሉበትን ሁኔታ በመገናኛ ብዙሃን ማየታቸውንና ለሌሎች ስራዎችም ትምህርት እንደሚሰጥ አስረድተዋል።

በኦሮሚያ የጉጂ ዞን ሸሪአ ፍርድ ቤት ተጠሪ ሼኸ ከድር አብዱራህማን ትናንት ምሽት በቴሌቭዥን የተመለከቱት የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት የወደፊት ብሩህ ተስፋን የሚያሳይ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል።

"ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ ተሰርቶ ለእይታ መብቃቱ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን በመሳብ የቱሪዝም ገቢንም ከማሳደግ በተጨማሪ ለሌሎች መሰል ስራዎችም ዓርአያ ነው" ብለዋል፡፡

"አላግባብ የሚባክን እውቀት፣ የተፈጥሮ ሀብት ጉልበትና ጊዜን ብንጠቀም መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ የምንሰለፍበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆንም ተስፋ ሰጭ ነው" ብለዋል።

በመልካም አስተዳደር ጉድለት በጉጂ ዞን ከ10 ዓመታት በፊት የተጀመሩና ያልተጠናቀቁ የገናሌ ነገሌ የመጠጥ ውሃና ሌሎች መሰል ፕሮጀክቶችም በዚሁ አግባብ ተሰርተው እንዲጠናቀቁ ጠይቀዋል። 

ሌላው የነገሌ ከተማ ነዋሪ አቶ ታምሩ ታዬ ፓርኩ የሀገራችንን መልካም ገጽታ በመቀየር የቱሪዝም ገቢን በማሳደግ ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

"ኢትዮጵያን ቀዳሚና ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ታላቁን የህዳሴ ግድብንና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶችን ጥቅም ላይ ለማዋል በሚደረገው ጥረትም ድጋፍ በማድረግ የድርሻዬን እወጣለሁ" ብለዋል፡፡

የተፈጥሮ ሀብትን ጥቅም ላይ በማዋል የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ ወጣቱ ስራ ፈጣሪ እንጂ ጠባቂ መሆን እንደሌለበት የሚያነሰሳ ስራ ሆኖ እንዳገኘው የተናገረው ደግሞ ወጣት መኮንን በቀለ ነው።

"ተባብረንና ተጋግዘን ከሰራን እውቀቱ ችሎታውና የተፈጥሮ ሀብቱ ያለን በመሆኑ በአጭር ጊዜ ከድህነትና ኋላቀርነት መውጣት እንደሚቻል ከዚህ ልምድ መወሰድ አለበት" ብሏል፡፡

በፕሮጀክቱ ለተሳተፉ አካላት ትናንት በተዘጋጀ የምስጋና ምሽት በቀረበው ዘጋቢ ፊልም ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አዎንታዊ ውጤት ከፍጻሜ ይደርስ ዘንድ፣ ጥቂት ቆራጦችን እንደሚጠይቅ ገልጸው መሰል ፕሮጀክቶችም በቀጣይ በክልሎች ለማከናወን መታቀዱን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም