የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የመሬት መረጃ በማምረት ለስነምህዳር ሚዛን መጠበቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው

82

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 9/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የመሬት አጠቃቀም መረጃ በማምረት ለስነምህዳር ሚዛን መጠበቅ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ገለጸ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቱሉ በሻ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በልየታ፣ ክትትል እና መሬት አጠቃቀም መረጃ በማምረት የዕቅድ ግብዓት አበርክቷል።

የአረንጓዴ አሻራ ዕቅድ የተዘጋጀው የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ ያስታወሱት ዶክተር ቱሉ፤ የጂኦስፓሻል ወይም አጠቃላይ የመሬት መረጃ አንዱና ዋናው ጉዳይ እንደነበር ገልጸዋል።

በተለይም የደን ሽፋን የሳሳባቸውን አካባቢዎች ለይቶ ማመላከትና ምን አይነት ዛፍ ከስነ-ምህዳሩ ጋር ይስማማል የሚለውን ለመለየት የመሬት መረጃ እጅግ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

እ.አ.አ ከ2003 ጀምሮ በየአምስት አመቱ የመሬት አጠቃቀም መረጃ ኢንስቲትዩቱ እያመረተ እንደሚገኝ ዶክተር ቱሉ ገልጸዋል።

በዚህ መሰረት ተቋሙ ከሁለት አመት በፊት ያመረተውን አገር ዓቀፍ የመሬት አጠቃቀም መረጃ ለአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በመስጠት ለአረንጓዴ አሻራ ስራ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

በዚህም የመሬት አጠቃቀም መረጃ በማምረት ለስነምህዳር ሚዛን መጠበቅ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የሚላኩ የመሬት አጠቃቀም መረጃ ሪፖርት መኖራቸውን ገልጸዋል።

ነገር ግን በዚህ ብቻ ሳይወሰን የብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ የሚተከሉ ችግኞችን በተመለከተ የማረጋገጥ ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ወደፊት በቴክኖሎጂ የታገዘ ስራ የሚሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 15 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱን የገለጹት ፕሮፌሰር ፍቃዱ፤ ይህ መረጃ በ2008 ዓ.ም በተደረገ ቆጠራ የተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

ያለፈውን ዓመት ጨምሮ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው የችግኝ ተከላ ዘመቻ ወደፊት በአገራዊ የደን ሽፋን ላይ አወንታዊ ውጤት እንደሚኖረውም ገልጸዋል።

የደን ሽፋን ቆጠራ በየአምስት ዓመቱ የሚከናወን ሲሆን በ2013 ዓ.ም እንደሚካሄድ የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም