ትረስት ፈንዱ ከ5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ለቀቀ

68

  አዲስ አበባ  ነሀሴ 9/2012  (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በመጀመሪያ ዙር ለመረጣቸው አምስት ፕሮጀክቶች ከ5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ መስጠቱን ገለጸ።

ገንዘቡን ለታለመለት ዓላማ ማዋል እንደሚገባም አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በመስከረም ወር 2012 ዓ.ም የቀረቡለትን 300 የፕሮጀክቶች ትልመ ሀሳብ (ፕሮፖዛል) ላይ ግምገማ አድርጎ በታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም 22 ፕሮጀክቶችን መለየቱ የሚታወስ ነው።

በ22ቱ ፕሮጀክቶች ላይ ዳግም ባደረገው ግምገማም ትረስት ፈንዱ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግላቸውን አምስት ፕሮጀክቶችን በየካቲት ወር 2012 ዓ.ም ይፋ ማድረጉም እንዲሁ።

በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በመጀመሪያ ዙር ድጋፍ ለሚያደርግላቸው አምስቱ ፕሮጀክቶች ከ5 ሚሊዮን 876 ሺህ ብር በላይ መልቀቁን ዛሬ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ከዚህ በፊት ገንዘቡ እንዲለቀቅ በትረስት ፈንዱ የዳይሬክተሮች ቦርድ ጸድቆ እንደነበረም አውስቷል።

የፈንዱ የአማካሪዎች ምክር ቤት ነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም በፕሮጀክቶቹና በፕሮጀክቶቹ አቅራቢዎች ላይ የመጨረሻ ዙር ግምገማ አድርጎ ገንዘቡ እንዲሰጥ መፍቀዱንም መግለጫው አመልክቷል።

በዚሁ መሰረት ገንዘቡ ነሐሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም በፕሮጀክቶቹ አስፈጻሚ ተቋማት የባንክ አካውንት እንዲገባ መደረጉን ነው ትረስት ፈንዱ በላከው መግለጫ ያስታወቀው።

ለድጋፍ የተመረጡት ፕሮጀክቶች ትረስት ፈንዱ የፕሮጀክት ሁኔታን ያሟላሉ ብሎ ያቀረባቸውን መስፈርቶች ማሟላት አለማሟላታቸውን በቴክኒክ ግምገማ ቡድኖች ጠንካራ ግምገማ እንደተደረባቸው ተገልጿል።

የተቋማቱ የሀብት፣ የአስተዳደርና ያቀረቡትን ዕቅድ የመፈጸም አቅም መፈተሹም መግለጫው አመልክቷል።

የፕሮጀክት ዘላቂነትና ቀጣይነት፣ ፕሮጀክቶቹ የሚያሳርፉት ተጽዕኖ፣ የማደግ አቅም፣ ፈጠራ፣ የሀብት አጠቃቀም፣ ተጠያቂነትና ግልጽነት የግምገማው ዋና ዋና መስፈርቶች ናቸው ተብሏል።

ሄልፕ ፎር ፐርስንስ ዊዝ ዲስኤበሊቲ ኦርጋናይዜሽን፣ ጉርሙ እና ህይወት ኢንቴግሬትድ የተሰኙ የልማት ተቋማት፣ ፕሮ ዲቨሎፕመንት ኔትወርክ እና ኮራ ግሬት ሆፕ የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት ገንዘቡ የተሰጣቸው ተቋማት ናቸው።

ፕሮጀክቶቹ ውሃ፣ ጤና፣ ንጽህና አጠባበቅና ትምህርት ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ አፋርና ትግራይ ክልሎች እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ ፕሮጀክቶቹ ተግባራዊ የሚሆንባቸው እንደሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ በውጭ አገር የሚኖሩ 26 ሺህ ኢትዮጵያዊያን እስካሁን ለትረስት ፈንዱ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

"ዓለም በኮቪድ-19 ምከንያት የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ በገባችበት በእዚህ ወቅት ዳያስፖራው እያደረገ ላለው  ድጋፍ የፈንዱ አማካሪ ምክር ቤትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የዳያስፖራው ማህበረሰብ ያበረከተው አስተዋጽኦ በዘላቂነት ውጤታማ እንዲሆን የፕሮጀክቱ ፈጻሚዎች ገንዘቡን ለታለመለት ዓላማ ማዋል እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

የፕሮጀክቱን ድጋፍ ያገኙት ተቋማት የትረስት ፈንዱ ዓላማዎች የሆኑትን የኢትዮጵያዊያንን ወሳኝ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት ፕሮጀክቶቹን ውጤታማና በተቀመጠው ጊዜ ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆን እንዳለባቸውም ትረስት ፈንዱ ገልጿል።

አምስቱ ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ 50 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ከዚህ በፊት ማስታወቁ አይዘነጋም ።

ለፕሮጀክቶቹ የሚደረገው የገንዘብ ድጋፉ ደረጃ በደረጃ እንደሚለቀቅና የተቀሩት 17 ፕሮጀክቶችም በአማካሪ ምክር ቤቱ የታየባቸውን ጉድለት ሲያሟሉ ከፈንዱ ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ወደ ሥራ እንደሚገቡም መግለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ከሁለት ዓመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ከጎበኙ በኋላ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በቀን ከሚጠጡት ማኪያቶ ላይ ቀንሰው አንድ ዶላር ለአገራቸው እንዲያዋጡ ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ የተመሰረተ ተቋም ነው።


እስካሁን በትረስት ፈንዱ አማካኝነት በውጭ አገር ከሚኖሩ 26 ሺህ ኢትዮጵያዊያን ከ6 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሰብሰቡ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም