ኮሮናን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ በማስተግበሩ በኩል ሰፊ ክፍተት መኖሩን አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ

67

አዳማ፣ ነሐሴ/09/2012(ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በትክክል በማስተግበሩ በኩል ሰፊ ክፍተት መኖሩን የጠቅላይ ሚኒስቴር ፕሬስ ሰክሬተሪያት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ።

የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በአዲስ መልክ የተጀመረውን ዘመቻ ለማሳካት እንዲያግዙ ለመገናኛ ብዙሃንና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች የተዘጋጀ የስልጠና መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሄዷል።

በመድረኩ የተገኙት አቶ ንጉሱ ጥላሁን በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት የኮሮና በሽታን ስርጭት ለመግታት የወጣውን አዋጅ በትክክል ከመተግበር አንጻር ሰፊ ክፍተት አለ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ባደረገው ጥናትና የመስክ ምልከታ በህብረተሰቡ መዘናጋትና በአስፈፃሚው ዘንድ ባለው ቸልተኝነት  አዋጁ መጣሱን አረጋግጧል ብለዋል።

በዚህም በሽታው በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እየተስፋፋ  በቀን ከ1ሺህ በላይ ዜጎች በቫይረሱ እየተያዙ መሆኑን አመላክተዋል።

የአዋጁን የክልከላ ድንጋጌዎች በሚጥሱት አካላት ላይ ለህዝብ ደህንነት ሲባል የእርምት እርምጃ በመውሰድ የባህሪ መጓደል ሁኔታዎች ማስተካከል አለብን ብለዋል።

"ዜጎች በወረርሽኙ ምክንያት እየሞቱ ነው "ያሉት አቶ ንጉሱ  የአብዛኛቹ ህይወት በቫይረሱ ምክንያት ማለፉን የተረጋገጠው በአስክሬን  ምርመራ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህን ችግር ለመግታት መንግስትና የኃይማኖት መሪዎችን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሀገራዊ ሃላፊነትን ለመወጣት በትብብርና ቅንጅት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

አሁን እየደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡ አካባቢ የታየውን የአስተምሮ መጓደል ማረም እንደሚገባም አመልክተዋል።

ስለ በሽታው በማወቅና በመገንዘብ ህዝቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ ጥሩ ቢሆንም በሽታውን ለመከላከል የተቀመጡ መመሪያዎች እየተተገበሩ እንዳልሆነ አቶ ንጉሱ ገልጸዋል።

እስካሁን በሽታውን ለመከላከል የተከናወነው ስራ  የቫይረሱ ስርጭት የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ መርዳቱን መደረጉንም የተናገሩት አቶ ንጉሱ የነበረው የአስተምሮ ሂደት በመለወጥ በህብረተሰቡ  ዘንድ የባህሪ ለውጥ ለማምጣት የመገናኛ ብዙሃንና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች ስራ መጠናከር አለበት ብለዋል።

የመድረኩ ዓላማ ቀጣይ የማስተማሪያ ዘይቤውን ለመፈተሽ፣ የጎደለውን ለመለየትና ችግሩን ለመፍታት የሚያግዝ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነው።

የጤና ሚኒስቴር ኮሙዩኒኬሽን  ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶክተር ተገኔ ረጋሳ በበኩላቸው ባለፉት ስድስት ወራት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት  ለህብረተሰቡን ስለበሽታው በቂ ግንዛቤ እንዲኖረውና ራሱን እንዲጠብቅ ከማድረግ አንፃር መገናኛ ብዙሀን ሚና እንደነበራቸው አውስተዋል።

ስልጠናው አሁን የተጀመረውን የምርመራና ማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄ ዘመቻን ግቡን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት በሙያቸው የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻሉ የተዘጋጀ መሆን ገልጸዋል።

ለሁለት ቀናት በተካሄደው የስልጠናው መድረክ  የመገናኛ ብዙሃንና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም