ወጣቶች ለተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ

85

አዲስ አበባ  ነሀሴ 9/2012  (ኢዜአ) በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የወረዳ 1 ወጣቶች ለተቸገሩ 1 ሺህ 100 ሰዎች  የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ አደረጉ። 

ከኢትዮጵያ ውጭ ከሚኖሩ የወረዳው ተወላጆች በተሰበሰበ ገንዘብ ድጋፍ የተደረገላቸው በኮሮናቫይረስ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ አባውራዎች እና እማውራዎች ነው፡፡

በእዚህም ለእያንዳንዳቸው ለአንድ ወር የሚሆን ሩዝ፣ ዱቄት፣ ዘይት እንዲሁም የንጽህና መጠበቂያ ሳሙና ተለግሷል፡፡

ለእያንዳንዱ ሰው የተደረገው ድጋፍ በገንዘብ ሲሰላ ከ1 ሺህ ብር በላይ ግምት እንዳለውም ነው በድጋፉ ወቅት የተገለጸው።

የወረዳው የማዕድ ማጋራት መርሃግብር ምክትል ሰብሳቢ እና የዳያስፖራ ተወካይ አቶ ፍሬዘር ሳላህ ድጋፉ ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገ መሆኑን አስታውሰዋል።

በድጋፉም የኮቪድ -19 መከሰትን ተከትሎ ለችግር የተዳረጉ አባውራና እማውራዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡

ለተቸገሩ ድጋፍ የማድረግ ሥራው ቀጣይነት እንደሚኖረውና ወደፊት ግብረሰናይ ድርጅት በመክፈት በስፋት የመንቀሳቀስ ዕቅድ መያዙንም ተናግረዋል።

ዛሬ ድጋፍ ከተደረገላቸው እማውራዎች አንዷ የሆኑት ወይዘሮ ጠይባ ሰኢድ በድጋፉ ደስተኛ መሆናቸውንና  ሌሎችም ከወጣቶቹ መልካም ተግባር በመማር ለተቸገረ እንዲደርሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የወረዳ 1 ምክትል ሥራ አስፈጻሚና የንግድና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደስታ አለሙ ኮቪድ- 19 በስፋት ከተከሰተባቸው የአዲስ አበባ አካባቢዎች አንዱ አዲስ ከተማ መሆኑን ተናግረዋል።

ችግሩን የተረዱ የወረዳው ተወላጅ ዳያስፖራዎችና ወጣቶች ችግረኞችን በማሰብ የፈጸሙት መልካም ተግባር ለሌሎች አርአያ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

በወረዳው ከማዕድ ማጋራት ተግባር በተጨማሪ በተለያዩ የበጎፈቃድ ሥራዎች የድሃ ድሃ በሚል ለተለዩ ነዋሪዎች ቤታቸውን የማደስ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ደስታ አመልክተዋል፡፡

በወረዳው ኮሮናቫይረስን ከመከላከል አንጻር የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመወ፣ የኢኮኖሚ አቅማቸው የተሻለ ደረጃ ላይ ያሉ ባለሃብቶች ያላቸውን በማካፈል ይሄን ጊዜ ተደጋግፎ ማለፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም