የተቋረጡት የእግር ኳስ ጨዋታ ውድድሮች ከ6 እስከ 8 ሳምንታት ሊጀመሩ ይችላሉ--- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን

215

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 9/2012(ኢዜአ) በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጡት የእግር ኳስ ጨዋታ ውድድሮች ከ6 እስከ 8 ሳምንታት ባሉት ጊዜያት ሊጀመሩ እንደሚችሉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

ፌደሬሽኑ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጡት የእግር ኳስ ጨዋታ ውድድሮች ዳግም የሚጀመሩበትን መመሪያና ደንብ ማውጣቱንም ገልጿል።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የክለብ ላይሳንሲንግ ዳይሬክተር ኢንስትራክተር ቴዎድሮስ ፍራንኮ እንደገለጹት፣ የጤና ጥበቃ ፈቃድ ከተገኘና የጋራ መግባባት ላይ ከተደረሰ የእግር ኳስ ጨዋታ ውድድሮቹ ከ6 እስከ 8 ሳምንታት ባሉት ጊዜያት ውስጥ ዳግም እንዲጀመሩ ይደረጋል።

በውድድሮቹም የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ፣ ከፍተኛ ሊግ፣ ብሔራዊ ሊግ፣ የሴቶች አንደኛ ሊግ እና ከ20 ዓመት በታች ተሳታፊ የሆኑ የሊጉ ቡድኖች ቅድመ ዝግጅት አድርገው እንደሚሳተፉ አመልክተዋል።

ውድድሮቹ በሦስት የተለያዩ ከተሞችና በስድስት ስታዲየሞች እንደሚደረጉ የጠቆሙት ኢንስትራክተር ቴዎድሮስ፣ ጨዋታዎችና ልምምዶች ከመጀመራቸው ከ72 ሰዓት በፊትም ለተጫዋቾች፣ አሰልጣኞችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የኮቪድ ምርመራ እንደሚደረግ ገልፀዋል።  

ፌደሬሽኑ የእግር ኳስ ውድድሮችን ዳግም ለማስጀመር ያወጣውን መመሪያ አስመልከቶ ሲገልጹም፣ መመሪያው ከጤና ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባባር የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

ማንኛውም የእግር ኳስ እንቅስቃሴዎች ከመጀመራቸው በፊት ኮቪድ -19ን ያማከለ የአሰራር ቅድመ ሁኔታዎች በዝርዝር ተቀምጠዋል።

ከቅድመ ሁኔታዎቹ ውስጥ የስልጠና እና የውድድር የጊዜ ሰሌዳ፣ የተጨዋቾች ዝውውርና የሥራ ኮንትራት የተመለከተ፣ የተጨዋቾች የልምምድና የስልጠና መመሪያ እንዲሁም የተጨዋቾች የጉዞና የውድድር ደንብ መመሪያ የሚጠቀሱ ናቸው።

መመሪያው የተጨዋቾች የሜዳ ውስጥ እንቅስቃሴ፣ የስነ ባህሪ እና የሥነልቦና ሁኔታ እንዴት መሆን እንዳለበት በዝርዝር የሚያትት መሆኑንም ኢንስትራክተር ቴዎድሮስ ገልፀዋል።

እንደ እሳቸው ገለጻ ከተጨዋቾች፣ አሰልጣኞች፣ ዳኞችና ድጋፍ ሰጪ አካላት በስተቀር ሌሎች በጨዋታና በስልጠና ጊዜ እንዲሳተፉ አይፈቀድም።

በስታዲየም ውስጥ ደጋፊዎችን ማሳተፍ በጥብቅ ስለመከልከሉ በመመሪያው ላይ መቀመጡንም ተናግረዋል።

በስታዲየም ውስጥ እንደወንበር፣ ጠረጴዛ፣ ኳስ፣ ቁምሳጥኖችና መሰል ቁሶች ለንክኪ የሚያጋልጡ በመሆናቸው በየቀኑ በፀረ ተህዋሲ ኬሚካል እንደሚፀዱ ገልፀዋል።

የመመሪያው ዋና ዓላማ የእግር ኳስ ጨዋታ ውድድሮች እና ልምምዶች ሲደረጉ የቫይረሱን ስርጭት በመግታትና በመከላከል ሊሆን እንደሚገባ መሆኑንም ኢንስትራክተር ቴዎድሮስ አስረድተዋል።

"በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው ሲገኝም አፋጣኝ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኝ የማመቻቸት እሳቤም አለው" ብለዋል።  

ባለፉት 5 ወራት ከኮቪድ-19 ወረረሽኝ ጋር በተያያዘ የእግር ኳስ ጨዋታ ውድድሮች እንዲቋረጡ መደረጉ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ጨዋታ ውድድሮች መመሪያ ላይ ላለፉት ሦስት ቀናት በካፍ አካዳሚ ሲያደርገው የነበረው ውይይት ዛሬ መጠናቀቁ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም