በህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርና ሰው ማገት ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ ስድስት ግለሰቦች ተቀጡ

102

መተማ ነሐሴ 9/2012(ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን በህገ ወጥ መሳሪያ ዝውውርና ሰው ማገት ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የተከሰሱ ስድስት ግለሰቦች እስከ 11 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና በገንዘብ መቀጣታቸውን የዞኑ አቃቢ ህግ መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ቢተው አሳየ ለኢዜአ እንደተናገሩት በህገ ወጥ መሳሪያ ዝውውር ጥፋተኞ ተብሎ ከተቀጡት መካከል  ቻላቸው ጨቅሉ  የተባለው ግለሰብ ይገኝበታል።

ግለሰቡ ሐምሌ 19/2012 ዓ.ም በመተማ ወረዳ  መንደር 6 በተባለው ስፍራ 368 ሽጉጦችን ኮድ 3 - 56079 አማ በሆነ አይሱዚ የጭነት ተሽከርካሪ   ሲጓዝ መያዙን አመልክተዋል።

ጨለማን ተገን በማድረግ ባደረገው የህገ ወጥ መሳሪያ ዝውውር በቀረበበት የሰውና የሰነድ ማስረጃ ጥፋተኛ መሆኑ ተረጋግጦበታል።

ግለሰቡ በድርጊቱ በመፀፀቱና የቀደመ የወንጀል ሪከርድ የሌለበት መሆኑ በቅጣት ማቅለያነት በመውሰድ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትናንት በዋለው ችሎት   በዘጠኝ ዓመት ፅኑ እስራትና አንድ ሺህ ብር እንዲቀጣ መወሰኑን አቶ ቢተው አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ ሰው በማገት ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የተከሰሱ አምስት ግለሰቦች  በቀረበባቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃ ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።

ግለሰቦቹ በሚያዝያ 15/2012 ዓ.ም መተማ ወረዳ መቃ ቀበሌ በሁለት ተሽከርካሪዎች አግተዋቸው በማጓገዝ ላይ  ከነበሩ ሰባት ሰዎች   ከእያንዳንዳቸው ከ100 ሺህ እስከ 150 ሺህ የሚደርስ ገንዘብ በመቀበል ወንጀል መፈፀማቸው በቀረበባቸው  ማስረጃ ተረጋግጠባቸዋል።

ክሳቸውንም ማስተባበል ባለመቻላቸው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትናንት በዋለው ችሎት አንደኛ ተከሳሽ  አየልኝ እያዩና ሁለተኛ ተከሳሽ መዝገቡ እያዩ በወንጀሉ በዋናነት ተሳትፎ እንደነበራቸው በማመሳከር    እያንዳንዳቸው በ11 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን የአቃቢ ህግ መምሪያው ኃላፊ ተናግረዋል።  

በድርጊቱ ተባባሪ ነበሩ የተባሉት ጓዴ ፈረደ፣ የኛነው አበበ እና  ገላጋይ ተገኘ ደግሞ እያንዳንዳቸው በአስር  ዓመት ፅኑ እስራት  እንዲቀጡ መወሰኑን  አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም