ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የልማት ፕሮጀክት ክልሎች ሊማሩ ይገባል- በአሶሳ አስተያየት ሰጪዎች

96

አሶሳ፣ ነሐሴ 09 /2012 (ኢዜአ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በአጭር ጊዜ ከተከናወኑ የልማት ፕሮጀክት የክልል አመራሮች ሊማሩ እንደሚገባ በአሶሳ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ነዋሪዎቹ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በአጭር ጊዜ ያከናወኗቸው ተግባራት የሚበረታታ ነው።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ አብዱልቃድር ነዳኔ  ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክት ባለፉት ሁለት ዓመታት ምን መሥራት እንዳለብን፣ ያለንን የሰው አቅም እና ዐብት መረዳት ችለናል ሲሉ ገልጸዋል።

እንደ መንግሥትም ሆነ ሕዝብ ከዚህ በኋላ መሥራት ያለበት ካደጉ አገራትና ዜጎች ጋር በማነጻጸር ሊሆን እንደሚገባ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መማር እንደሚቻል ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቶች በየአካባቢያችን አሻግረን ባለማየት እየጀመርን የምንተዋቸውን እንዲሁም ያሉንን የተፈጥሮ ሀብቶች ያሳየ ነው ያሉት ደግሞ አቶ ዓለምብርሃን ዱጉማ  ናቸው።

መለወጥ ቅርብ እንደሆነ መረዳት እንደቻሉ ገልጸዋል።

በተለይም የክልል አመራሮች ሀሳብ በማፍለቅና በአነስተኛ በጀት ወጣቱን አስተባብረው የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ውጤት ማምጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ሊሠራበት የሚገባ እንደሆነ አቶ ዓለምብርሃን  አንስተዋል።

ወጣት ሰንበቶ ሞሲሳ በበኩሉ  በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተከናወነው ፕሮጀክት ከሕዳሴው ግድብ ውኃ ሙሌት ቀጥሎ እጅግ ያስደሰተኝ ነው ሲል ተናግሯል።

ፕሮጀክቱ ፖለቲካ ሳይሆን በተግባር የታየ ልማት መሆኑን ገልጾ "የመሥራት አቅም የሌላቸው ሰዎች ይተቻሉ "ብሏል።

ፕሮጀክቱ ዕውቀትና ሀብት ላላቸው ዜጎች መነሻ ሃሳብ እንደሰጠ ያመላከተው ወጣት ሞሲሳ በጋራ ከተሰራ መሰል በርካታ ፕሮጀክቶችን በሀገሪቱ በተያዩ አካባቢዎች ማስፋፋት እንደሚቻል ያስተማረ መሆኑን ገልጿል።

በቤተ-መንግሥት ብቻ የዓለምን ቀልብ የሚገዙ ሀብቶችን ይዘን ሳንሰራ መኖራችንን የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ፕሮጀክት ማሳየቱን የተናገረው ደግሞ ወጣት ታደሰ ቢራቱ ነው።

"የዜጎችን የፈጠራ አቅም ለማጎልበት በየአካባቢው የንባብ ማዕከላትን ማዳበር ይጠበቅብናል" ያለው ወጣቱ የክልል አመራሮች ከፕሮጀክቱ ሊማሩበት እንደሚገባ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም