ዳሸን ባንክ ሥራ ፈጠራን የሚያበረታታ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ

91

ባሕርዳር/መቀሌ፣ ነሐሴ 9/2012(ኢዜአ) ዳሸን ባንክ የወጣቶችን የሥራ ዕድል ፈጠራን ''የኢትዮጵያ ታለንት ፓዎር ሲሪየስ'' ፕሮጀክቱን በአማራና ትግራይ ክልሎች ይፋ አደረገ።

በባንኩ የባሕርዳር ቅርንጫፍ ሥራአስኪያጅ አቶ እሸቴ ትናንት ማምሻውን በሰጡት መግለጫ"ፕሮጀክቱ በሀገሪቱ ሥራ ፈጠራን ለማበረታታትና ክህሎት ላላቸው ዜጎች የፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርግ ነው ብለዋል"።

ባንኩ በሀገሪቱ በተመረጡ ከተሞች ከታኅሣሥ ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ የሀገሪቱ ዜጎች የሚሳተፉበት የማኅበራዊ መዋዕለ ንዋይ ይፋ ተደርጎ እየሰራ እንደሚገኝ አውስተዋል።

በዚህ መረሃ-ግብር መሠረት ዘንድሮ አዲስ አበባንና ባሕርዳርን ጨምሮ በተመረጡ ስድስት የሀገሪቱ ከተሞች የሚገኙ ዜጎች ተመልምለው የሥራ ፈጠራ ክህሎትና የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ለመስጠት አቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሥልጠና የሚወስዱ አካላት ባንኩ ባለፈው ታኅሣሥ ወር ይፋ ያደረገውን የሥልጠና መስኮች መሠረት አድርገው ሥራ ፈጥረው ለመሥራት ፍላጎት ያላቸውን ወጣቶች ያሳትፋል።

ከእያንዳንዱ ከተማ 100 የሥራ ፈጠራ ተጠቃሚዎችን በመመልመል አስፈላጊ ሥልጠናዎች በመስጠት የመቋቋሚያ ገንዘብ ይሰጣል።

በባሕርዳር ከተማም ከነሐሴ 11 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ቀናት ለ100 የሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚዎች ሥልጠና ይሰጣቸዋል።

ሥልጠናውን ያገኙ ዜገችም በአማካሪ ድርጅቶች እየታገዙ የቢዝነስ ክለብ በማቋቋም ሥራ ለመጀመር የሚያስችል ድጋፍ ከባንኩ እንዲያገኙ ይደረጋል።

እንደ ሀገር 100 ሚሊዮን ብር የተመደበለት ይህ ፕሮጀክት ከሚያተኮርባቸው የሥልጠና ዓይነቶች መካከል የሥራ ፈጠራ፣ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አቅም ግንባታ፣ የከፍተኛ ትምህርት የፋይናንስ ድጋፍ መረሃ-ግብር፣ የፋይናንስ ተደራሽነት መረሃ-ግብርና ስለቢዝነስ ክለብ ምሥረታ ይገኙበታል።

ዓላማው የሥራ አጥነትን በመቀነስ  ድህነትን ከሀገሪቱ ለማስወገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ መሆኑ አቶ እሸቴ አብራርተዋል።

በተመሣሣይ ፕሮጀክቱ በትግራይ ክልል ይፋ ሲደረግ በዳሽን ባንክ የመቀሌ ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ ብርሃኑ "ፕሮጀክቱ ሥራ ፈጠራን በማበረታታትና ክህሎት ላላቸው ዜጎች የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ሥራ አጥነት ለመቀነስ ይሰራል "ብለዋል።

በትግራይ ክልል 600 ሥራአጥ ወጣቶችን በማወዳደር ያሸነፉ 100 ወጣቶች በ"ቴሌግራም" እና "ኦንላይን" ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ለአምስት ቀናት ሥልጠና ይሰጣል።

ሥልጠናው ያገኙት ዜጎችም በአማካሪ ድርጅት እየታገዙ የንግድ ክለብ እንዲያቋቁሙ ይደረጋል ያሉት አቶ አሸናፊ ሥራ ለመጀመር የሚያስችል ድጋፍ ባንኩ እንደሚያመቻች አስታውቀዋል።

ፕሮጀክቱ እስካሁን  በሐዋሳ፣ አዳማና ድሬዳዋ ሥልጠናውን በመስጠት ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መገባቱም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም