የአማራ ክልልና ገቢዎች ሚኒስቴር በአፋር ክልል ጎርፍ ጉዳት ላደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ አደረጉ

102

ሠመራ ነሐሴ 9/2012 (ኢዜአ) - የአማራ ክልላዊ መንግሥትና የገቢዎች ሚኒስቴር በአፋር ክልል ጎርፍ ጉዳት ላደረሰባቸው ወገኖች ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብና አልባሳት ድጋፍ አደረጉ።

ሠመራ ከተማ በመገኘት ዛሬ ድጋፉን ያደረጉትና ሌሎችም አካላት በጎርፍ የተጎዱ አካባቢዎችንም ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ድጋፉን ለአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር  አቶ አወል አርባ ባበረከቱበት ወቅት እንደተናገሩት ካሙጡት ድጋፍ ውስጥ 500 ብርድ ልብስ፣ 500 ጥንድ አንሶላዎች፣ 500 ፍራሽና 1 ሺህ 500 ኩንታል የምግብ እህል ይገኙበታል።

ሁላችንም የሉሲ ልጆች በመሆናችን የአፋር ሕዝብን መደገፍ የራሳችንን ሕዝብ እንደመደገፍ ነው ያሉት አቶ ተመስገን በቀጣይም በጎርፍ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እስኪመለሱ ድጋፉ እንደሚቀጥል  አስታውቀዋል።

የተደረገው ድጋፍ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት መሆኑን አቶ ተመስገን አመልክተዋል።

የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው  በክልሉ በጎርፉ አደጋ በደረሰው ጉዳት የተሰማቸውን ሀዘን በመግለጽ መሥሪያ ቤታቸው ከአፋር ክልል ከጎን መሆኑን  ለማሳየት መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ በተለያዩ ጊዜያት በክልሎች ተከስተው በነበሩ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ድጋፍ ሲያደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በአፋር ክልል ጎርፍ ጉዳት ላደረሰባቸው ወገኖች ደግሞ አሁን ከ46 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ልዩ ልዩ አልባሳት፣ ስኳር፣ የምግብ ዘይት፣ ሩዝ፣ ዱቄትና ፓስታ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው በቀጣይም እንደሚያግዙ አስታውቀዋል።

የአፋር ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በክልሉ የተከሰተው ጎርፍ ከዚህ በፊት ታይቶ እንደማይታወቅ ገልጸው በዚህም ሳቢያ የተጎዱ ወገኖችን ለመታደግ የሀገር መከላከያና አየር ኃይል ንቁ ተሳትፎና ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

በዚህም  በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ምግብ በማድረስና በውኃ የተከበቡ ሰዎችን በሄሊኮፕተር በማውጣት ያበረከቱት አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን አውስተዋል።

ሁሉም ክልሎችና የፌዴራል መንግሥት ተቋማት በጎርፉ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች  ምላሽ ለመስጠት የሚያግዙ ድጋፎችን እያደረገ በመሆኑ በክልሉ ሕዝብና መንግሥት ሥም ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።

"ይህም ሁላችንም በአንድ ላይ ስንቆም ችግሮችን በራሳችን አቅም መፍታት እንደምንችል ማሣያ ነው፤ ወንድማማችነትንና አንድነቱን የሚጠናክር  ነው" ብለዋል።

በድጋፍ አሰጣጡ ሥነ ሥርዓት የተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግን ጨምሮ የሌሎችም ተቋማት ተወካዮች የተገኙ ሲሆን በጎርፍ የተጎዱ አካባቢዎችንም ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም