የዓለም ጤና ድርጅት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ ገለጸ

92

ሐረር ነሐሴ 9 / 2012(ኢዜአ)  የኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ   በዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮዽያ ኃላፊ ገለጹ፡፡

በኃላፊው  ዶክተር ቡሬማ ሀማ ሳምቦ የተመራው ልኡካን ቡድን የሀረሪ ክልል ቫይረስን ለመከላከል እያተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ተመልክቷል፡፡

በዚህ ወቅት እንደተናገሩት በክልሉ ወረርሽኙን ለመከላክል በየደረጃው እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች ናቸው።

ይህም ሆኖ በተለይም የቅኝት ስራዎችን ከማጎልበት አንፃር ትኩረት መስጠት አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እያደረጋቸው ያሉትን ስራዎች ለማገዝ  የአለም ጤና ድርጅት እንዲደግፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ  ዶክተር ቡሬማ ሀማ ሳምቦ ገልጸዋል።

የሐረሪ ከልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ፈትሂ መሃዲ በበኩላቸው ክልሉ በሽታውን ለመከላከል  ከአጎራባቾቹና የተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተለይም የኮሮና ቫይረስ እንደ ሀገር መከሰቱን ተከትሉ በክልሉ  የተለያዩ ተቋማት በአባልነት ያቀፈ ግብረ ኃይል በማቋቋም  ለመከላከል ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

ህብረተሰቡም እራሱን ከበሽታው እንዲጠብቅ ከኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች ወጣቶችና ሌሎች ተሰሚነት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመቀናጀት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና ቅስቀሳ እየተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህም ሆኖ አሁንም   በህብረተሰቡ ዘንድ  መዘናጋት ቸልተኝነት እንደሚስተዋል ጠቁመዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ከዚህ ቀደም በክልሉ ወባን ጨምሮ ሌሎችም ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመቆጠጠር እገዛ ሲያደርግ መቆየቱን ያወሱት አቶ ፈትሂ በቀጣይም ኮሮናን ለመከላከል ክልሉ የሚያደርገውን ጥረት እንዲደግፍም ጠይቀዋል።

በክልሉ ከሚገኙ ጤና ተቋማት ጋር በመቀናጀትና የመረጃ ስርዓትን በማጎልበት አፋጣኝ ምላሽ የመስጠት ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በክልሉ ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥርና ምርምር ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ተፋ ናቸው።

ተቋማትን በተለይም የለይቶ ማቆያ እና ማከሚያ ተቋማት የማዘጋጅት እንዲሁም የቅኝት ስራዎች  ሲከናወኑ ቆይተዋል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች የተጠናከረ የማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄና ምርመራ ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም