ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ኮቪድ-19ን ለመከላከል ድጋፍ እያደረገ ነው

88

 አዲስ አበባ  ነሀሴ 9/2012  (ኢዜአ) የዳያስፖራው ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል በገንዘብና በእውቀት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኮሮናቫይረስ በቻይና ሁቤይ ግዛት ውሃን ከተማ ከተከሰተበት ታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ ቫይረሱ በፍጥነት በመዛመት ሚሊዮኖችን አጥቅቷል፤ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችንም ህይወት ቀጥፏል።

መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ከቡርኪናፋሶ የመጣ ጃፓናዊ ዜጋ በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዘ የመጀመሪያ ሰው ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን ቫይረሱም በአሁኑ ወቅት በስፋት እየተሰራጨ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ቫይረሱ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ኤጀንሲው ከኤምባሲዎችና ሚሲዮኖች ጋር በመሆን በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መልዕክት ሲያስተላለፍ መቆየቱን ይገልጻሉ።

የኮሮናቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት ጊዜ አንስቶ በአገር ውስጥ ላሉ ዜጎችና በውጭ አገር በቫይረሱ ምክንያት የኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ለገቡ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በአፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው ጉዳት ለከባድ የኑሮ ችግር የተጋለጡ ዜጎችን ወደ አገር ውስጥ የመመለስ ተግባር መከናወኑንና አሁንም መቀጠሉን አመልክተዋል።

"በኢትዮጵያ ቫይረሱን ለመከላከል በተቋቋመው ብሔራዊ የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ስር ባሉ ንዑስ ኮሚቴዎች ውስጥ ኤጀንሲው ከዳያስፖራው ሀብት የማሰባሰብ ኃላፊነት ተሰጥቶት እየሰራ ይገኛል" ብለዋል።

በኢትዮጵያ ቫይረሱ በገባ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት ከዳያስፖራው በገንዘብና በአይነት ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት መሰባሰቡንና ድጋፉም እየቀጠለ እንደሚገኝ ነው ወይዘሮ ሰላማዊት የገለጹት።

በገንዘብና በአይነት ከተደረገው ድጋፉ ባለፈ በዳያስፖራው ማህበረሰብ ለኮሮናቫይረስ ህሙማን ሕክምና  የሚሰጡ ባለሙያዎችና ምሁራን በጥናትና ምርምር የተደገፉ ስራዎችን እያከናወኑ መሆኑንም ዳይሬክተሯ አመልክተዋል።

ወይዘሮ ሰላማዊት እንዳሉት በአውሮፓና በአውስትራሊያ የሚገኙ ባለሙያዎችም የተለያዩ መተግበሪያዎችን ተጠቅመው የተለያዩ ውይይቶችን በየጊዜው በማድረግ ሳይንሳዊ ምክረ ሀሳቦችን እያቀረቡ ይገኛሉ።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በጤና ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት ባለፈ በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና በሌሎች መስኮች የሚያደርሰውን ጉዳት በማመላከት መፍትሔ ጠቋሚ የሆኑ ትንተናዎች በባለሙያዎች እየቀረቡ እንደሆነም ተናግረዋል።

መንግስት ከጠበቀው በላይ ሊባል በሚችል መልኩ የዳያስፖራው ማህበረሰብ ኮቪድ-19 ለመከላከል እያደረገ ያለው ድጋፍ ውጤታማና አስደሳች መሆኑን ነው ወይዘሮ ሰላማዊት ያስረዱት።

የኮሮናቫይረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሆነ በኢትዮጵያ ስርጭቱ እየሰፋ በመምጣቱ ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስፈልጉ የህክምና ቁሶችን ማሟላት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

ከዚህም አኳያ በኢትዮጵያ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል የሚያስፈልጉ የህክምና ግብአቶች ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱንና በዚህ ረገድ ዳያስፖራው የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቫይረሱን ለመግታት አጋዥ የሚሆኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎችና የውይይት መድረኮች በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

የጤና ስርአቱ ወረርሽኞችን ለመከላከል ያለው ምላሽና ዝግጁነትን የማሳደግ እንዲሁም  ኮቪድ-19 በተለያዩ መስኮች የሚያደርሰውን ጉዳት መቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ጉዳይ ልዩነት ሳይፈጥር በጋራ መቆም እንዳለበትም ወይዘሮ ሰላማዊት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም