አሸንድዬ፣ ሻደይና ሶለል የልጃ ገረዶች ባህላዊ ፌስቲቫል በዓልን ከኮሮና በማያገልጥ መልኩ እንደሚከበር ተገለጸ

54

ባህርዳር፣ ነሃሴ 9/2012 አሸንድዬ፣ ሻደይና ሶለል የልጃ ገረዶች ባህላዊ ፌስቲቫል በዓልን ለኮሮና በማያገልጥ መልኩ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

በዓሉ “ለጥንቃቄ የምናደርገው መራራቅ የዘላቂ አብሮነታችን መሰረት ነው” በሚል መሪ ሀሳብ ከነሐሴ 16 እስከ 21/2012 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ተመልክቷል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እየጨመረ መምጣት በባህላዊና ኃይማኖታዊ ክዋኔዎች ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።

ቢሮው የኮሮና ቫይረስ የሚያደርሰውን ችግር በመገንዘብ የወንድ ወጣቶችና የልጃገረዶች ክዋኔ በዓላት ከወትሮ በተለየ መልኩ እንዲከበሩ አቅጣጫ አስቀምጣል።

በዓሉም የአሸንድዬ፣ ሻደይና ሶለል ባህላዊ ክዋኔ የሚያሳይ "ዶክሜንታሪ "ፊልም በማቅረብ፣ የፓናል ውይይትና ዓውደ ርዕይ በማዘጋጀት የበዓሉን እሴትና ጸጋ ለሌላው በማስገንዘብ እንደሚከበር ገልጸዋል።

በተጨማሪም የአረንጓዴ አሻራ ራዕይን ለማሳካት የሚያስችል ችግኝ በመትከልና ደም በመለገስ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

ቀደም ሲል በሰሜን ወሎና ዋግ ኽምራ ዞኖች ይከበር የነበረው የልጃ ገረዶች በዓል ባለፉት ቅርብ ዓመታት በምስራቅ ጎጃም፣ አዊ፣ ደቡብና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች በልዩ ልዩ ስያሜ በማክበር ክልላዊ እንዲሆን መደረጉን አቶ እንድሪስ አውስተዋል።

ኮሮና በፈጠረው በዚህ አስቸጋሪ ዘመን በዓሉን ማክበር ያስፈለገበትም በህዝቡ ያለውን ስሜት እንዳይቀዘቅዝ በማድረግ በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የተያዘውን ግብ ለማሳካት መሆኑን አስታውቀዋል።

በዓሉን በአደባባይም ሆነ በሰፈር ልጆችም ሆኑ ወጣቶች ተሰባስበው በማክበር ለኮሮና እንዳይጋለጡ እስከ ታች ያለው የቢሮው መዋቅር ከኮሮና መከላከል ግብረ ኃይልና ከአካባቢ ሽማግሌዎች ጋር በመሆን እየተሰራ ይገኛል።

የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሃይለኢየሱስ ፍላቴ በበኩላቸው የአሸንድዬ፣ ሻደይና ሶለል የልጃገረዶች በዓል በክልሉ ከተለዩ 18 የመስህብ ሃብቶች አንዱ ለመሆን በቅቷል ብለዋል።

ይህን የልጃገረዶች እሴትና የነጻነት መገለጫ የሆነውን በዓል በኢትዮጵያና በሌሎም ዓለም  በማስተዋወቅ የቱሪስት መስህብ ለማድረግ መሰራቱን ተናግረዋል።

ሆኖም  በአሁኑ ወቅት የኮሮና ቫይረስ ከመከሰቱ ጋር ተያይዞ የውጭና ሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ባይመጡም በዓሉ በሰቆጣ፣ ላሊበላና ቆቦ ከተሞች ኮሮናን በመከላከል ይከበራል ብለዋል።

ነሐሴ 13/2012 ዓ.ም የሚከበረው ቡሄ የወንድ ወጣቶች በዓልም በጋራ በመሰባሰብ በአደባባይ የማይከበር መሆኑን አስታውቀዋል።

የየአካበቢው ህብረተሰብም ከቢሮው የተሰጠውን አቅጣጫ መሰረት አድርጎ በዓሉን በማክበር ራሱን፣ ቤተሰቡንና አካባቢውን ህዝብ እራሱን ከኮሮና ቫይረስ መጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም