ችግር በሚፈጥሩ አመራሮቹ ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ፓርቲው አስታወቀ

57

ጅማ፣ ነሐሴ 8/2012 (ኢዜአ) ተጻራሪ የፖለቲካ አቋም በመያዝ ችግር በሚፈጥሩ አመራሮቹ ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ የጅማ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ፡፡

ፓርቲው በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ለሁለት ቀናት ሲያካሄድ የቆየው  ውይይት ዛሬ አጠናቋል፡፡

በከተማው የብልጽግና ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ታሪኩ ለገሰ ውይይቱን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ  በውይይቱ መድረክ በከተማው የሚገኙ  የፓርቲው አንዳንድ አመራሮች ተጻራሪ የፖለቲካ አቋም በመያዝ ችግር እንደሚፈጥሩ በግምገማ ማወቅ ተችሏል ብለዋል፡፡

ከአሁን በኋላ ሁለት ቦታ ረግጦ ህዝብን ማገልገል በፍጹም እንደማይቻል ፓርቲው ካደረገው ውይይት በመነሳት አቋም መያዙንም ገልጸዋል፡፡

በዚሁም  ከጠላት ጋር በመቀናጀት የጸጥታ ችግር  የሚፈጥሩ አመራሮች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም የመልካም አስተዳደርና የሌብነትን ችግር ለመፍታት  አቅም የሌለውን አመራር በመለየት በሚመጥነው ስፍራ እንዲቀመጥ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አካባቢ ህብረተሰቡን ሆን ብለው በማመላለስና በማጉላላት ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚሰሩ አካላት መኖራቸው  መረጋገጡን ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም በእነዚህ አካላት ላይ የማስተካከያ እርምጃ የሚወሰድ በመሆኑ ህብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበርም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ፓርቲው በሚመራው መንግስት በከተማው የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የማድረግና የፋይናንስ አጠቃቀምን ትክክለኝነት የማጣራት ስራ በተገቢው ሁኔታ እንዲመራ ይደረጋልም ብለዋል፡፡

ከስራ እድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ ተገቢ ያልሆነ አሰራር በተከተሉ አመራሮች ምክንያት ለከተማው ወጣቶች ስራን በበቂ ሁኔታ መፍጠር ያልተቻለ መሆኑን አመልክተዋል።

በዚህም በርካታ የመስሪያ የመሸጫ ሼዶች  የወሰዱ አካላት መኖራቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች የተገኙ በመሆኑ በተገቢው በማጣራት ማስተካከያ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

በህጋዊነት ሼድ ከተረከቡ አንዳንድ ወጣቶች ደግሞ ከመስራት ይልቅ ከተማውን በመበጥበጥ ስራ ላይ የሚሳተፉ መኖሯቸው የተረጋገጠ በመሆኑ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ በውይይቱ አቋም መያዙን አስረድተዋል።

የአባ ጅፋር እግር ኳስ ስፖርት ክለብም ለተጫዋቾቹ ደሞዝ ለምን መክፈል እንዳልቻለና የገንዘብ አጠቃቀሙ ትክክለኝነት እንደሚጣራም እንዲሁ፡፡

በከተማው ደረጃ የፋይናንስ አወጣጥ ትክክለኝነትንና የመሬት ስርቆትን የሚያጣሩ ሁለት ኮሚቴዎች ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ መቋቋሙን አቶ ታሪኩ አስታውቀዋል፡፡

ውይይቱ  በከተማው ቀበሌዎች  አመራሮች ደረጃም መቀጠሉም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም