በቀጣዮቹ ሁለት ወራት መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ተጠናክሮ ይቀጥላል

80

አዲስ አበባ ነሀሴ 8/2012 (ኢዜአ) በቀጣዮቹ የነሐሴና መስከረም ወራት መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

ባለፉት የክረምት ወራት በአብዛኞቹ የአገሪቱ አካባቢዎች መደበኛ እና በአንዳንድ የደቡብ ምዕራብ፣ መካከለኛ እንዲሁም የደቡብ ደጋማ ቦታዎች ላይ ከመደበኛ በላይ ዝናብ ተስተውሏል።

በዚህም ወቅቱ የዝናብ መጠናከር የተስተዋለበትና የዳመና ሽፋን መቆየት የታየበት እንደነበር የኤጀንሲው መረጃ አመላክቷል።

መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ መጣል የታየበት የአየር ሁኔታ ለግድቦች ውሃ መሙላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገ እንደነበር የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ ይገልጻሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ የወንዞች ከመጠን በላይ መሙላትን እና ቅፅበታዊ ጎርፍን ያስከተለ እንደነበርም ተናግረዋል።

በተለይም በሃምሌ ወር በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ላይ የተስፋፋ የደመና ሽፋንና የዝናብ መጠን ተስተውሎ እንደነበር ጠቁመዋል።

በመሆኑም በቀሪው የክረምት ወራት (ነሐሴና መስከረም) መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በተለይም በሰሜን ምዕራብና በምዕራቡ የአገሪቱ አካባቢዎች በአብዛኛው መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይጠበቃል ነው ያሉት።

በአብዛኛው ደቡብ ምዕራብ፣ በመካከለኛው ምስራቅና የደቡብ ደጋማ የአገሪቷ አካባቢዎች እንዲሁም የሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይዘንባል ብለዋል።

በሚቀጥሉት የክረምት ወራት የአየር ሁኔታው ተጠናክሮ የሚቀጥል በመሆኑ "ነጎድጓድ አዘልና በረዶ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ" ሊከሰት ይችላል።

በመሆኑም በረባዳማ ቦታዎችና ጎርፍ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች ላይ የወንዞች ከመጠን በላይ መሙላት እና ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል ማህበረሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም