በህዳሴው ግድብ ላይ የተሻለ እውቀትና ተመሳሳይ አቋም ሊኖረን ይገባል-- የዲያስፖራ አባላት - ኢዜአ አማርኛ
በህዳሴው ግድብ ላይ የተሻለ እውቀትና ተመሳሳይ አቋም ሊኖረን ይገባል-- የዲያስፖራ አባላት
አዲስ አበባ ነሐሴ 8/2012 (ኢዜአ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጉዳይ ትክክለኛ መረጃ በመያዝ ለግንባታው ስኬት የጋራ ጥረት ማድረግ ይገባናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዲያስፖራ አባላት ተናገሩ።
የትዮጵያ የዲያስፖራ ኤጀንሲ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ዛሬ ለዳያስፖራ አባላት ስልጠና ሰጥቷል።
ስልጠናው የዲያስፖራ አባላቱ በግድቡ ዙሪያና የሃገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም በማስከበር ረገድ የሚያደርጓቸው ጥረቶች የተናበቡና የተቀናጁ እንዲሆኑ ለማስቻል ነው ተብሏል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የስልጠናው ተሳታፊዎች፤ በህዳሴው ግድብ ላይ በቂ እውቀት በመያዝ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ የማሳወቅና አወንታዊ ተፅዕኖ ለመፍጠር በጋራ ልንቆም ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን በጋራ የጀመሩት ግዙፍ ፕሮጀክት ለፍፃሜ እንዲበቃ መረባረብ ሲገባ በፖለቲካ ልዩነትና በሌሎች ምክንያቶች አቋማችን ሊሸረሸር አይገባም ብለዋል።
በኢትዮጵያ አሁን ላይ በርካቶች ጠንካራ ሀገራዊ ስሜት ኖሯቸው በጋራ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የዳያስፖራ አባላቱ ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በተለይ ዳያስፖራው በየትኛውም የዓለም ክፍል የአገሩ አምባሳደር በመሆን ለብሄራዊ ጥቅሟ ለመስራት ዝግጁ መሆን ይኖርበታል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በተለይም በአባይ ወንዝ ላይ ሊኖራት ስለሚገባው ጥቅም የማስረዳትና የማሳመን ሥራ ከዳያስፖራው ይጠበቃል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በቀጣይ ለምታደርጋቸው ድርድሮችና ብሄራዊ የመብት የማስጠበቅ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች የዳያስፖራው ሚና ሊጠናከር ይገባል ብለዋል አስተያየት ሰጪዎቹ።