ነባሩን የፍትሐ ብሔር ህጎችን ለማሻሻል እየተሰራ ነው

116

አዳማ ነሐሴ 08/2012 (ኢዜአ) ነባሩን የፍትሐ - ብሔር ህጎችና አሠራሮችን ለማሻሻል እየተሠራ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።

በፌዴሬሽን ምክር ቤት እየተዘጋጁ ባሉት የግብርና ምርትና ግብይት ትስስር ውል ስምምነትና ጤና መድህን ሽፋን ረቂቅ አዋጆች ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዳማ ከተማ ውይይት ተካሂዷል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤው በውይይት መድረኩ እንደገለጹት፤ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር እንዲቻል ነባሩን የፍትሐ ብሔር ህጎችና አሰራሮችን ለማሻሻል እየተሠራ ነው።

አዋጆቹ በሀገር አቀፍ ደረጃ መውጣታቸው ለክልሎች የተሻለ ጥቅም የሚያስገኙ  መሆናቸውን አመልክተው፤ ወጥነት ያለው የፍትሃብሔር ህጎችና አሠራር ከመዘርጋት አንፃር ረቂቅ አዋጆቹ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።

በዚህም የአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ፣ ኑሮውን ለማሻሻል፣ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማፋጠን ብሎም በአምራች አጋዥ ኩባንያዎች መካከል አስገዳጅ የህግ ማእቀፍ እንዲኖር ነው ብለዋል።

ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ረቂቅ አዋጅ የጤና አገልግሎቶች ጥራትና ፍትሃዊነት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እኩል ተደራሽ ለማድረግ ጭምር እንደሆነም  አፈ ጉባኤው ገልጸዋል።

በዚህም የማህበረሰብ  አቀፍ የጤና መድህን ሽፋን አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግና በሁሉም የጤና ተቋማት ደረጃ ጥራትን ለማስጠበቅ፣ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖርና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ መሆኑን አመልክተዋል።

አዋጁ የክልሎች የወሰን አስተዳደር የማይገድባቸውን የአግሮ ፕሮሰስንግ ኢንዱስትሪዎች የግብዓት ፍላጎት ለማሟላት፣ የውጭ ኩባንያዎች የሚፈልጉትን ህግ ሀገሪቷ እንዲኖራት የሚያስችል መሆኑን የገለጹት ደግሞ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ ናቸው።

"አዋጁ በፌዴሬሽን ምክር ቤት መዘጋጀቱ ክልሎችን እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፤  ከግብርና ልዩ ባህሪ ጋር የሚሄድ የፍትሐ ብሔር ህግ ነው" ብለዋል።

የግብርና ሴክተር ለሰው ሰራሽና ተፈጥሮ አደጋ የተጋለጠ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፤ አዋጁ አርሶ አደሩ ከኩባኒያዎች ጋር የመደራደር አቅማቸውን ለማሳደግና ነበሩን ህግ ለመተካት እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

በዚህም በአምራቹና በዘር አቅራቢ ድርጅቶች መካከል ግልፅ የሆነ የውል ስምምነት እንዲኖር፣ ለምርት ጥራት ፣ አዋጨነትና የገበያ ተደራሽነት በትብብር ለመሠራት ወሳኝ ሚና  እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

ዘለቄታዊ አጋርነት የሚያረጋግጥ ከመሆኑም ባለፈ የአምራችና የገዥ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ የምርት ሂደት፣ የቴክኖሎጅ አጠቃቀምና የግብይት ትስስር ለማረጋገጥ ጭምር እንደሆነ  ገልጸዋል።

ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ረቂቅ አዋጁ ህብረተሰቡ በሁሉም የጤና መዋቅር ውስጥ ወጥ የሆነ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚረዳ  መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  የጤና መድህን ኤጄንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አለሙ አኖ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የአባልነት ሁኔታን በመለወጥ ሁሉም ዜጎች የመድህን ሽፋኑ አባል እንዲሆኑ የሚያስገድድና የተበታተኑ ቋቶችን ለመሰብሰብ የሚረዳ  መሆኑንም አስረድተዋል።

"አዋጁ  የውጭ እና የሀገር ውስጥ ተሞክሮን ያካተተ በመሆኑ በፌዴራልና ክልሎች ደረጃ የጤና መድህን ሸፍን ቀጣይነት ፣የአገልግሎት ጥራትና ተጠቃሚነት በሶስተኛ ደረጃ ሆስፒታሎች ጭምር ተደራሽ ለመሆን ያስችላል "ብለዋል።

ለአንድ ቀን በተካሄደው የውይይት መድረክ ከአስር ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ባለደርሻ አካላት ተሳትፈዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም