የኦብነግ መሪዎች የይቅርታና የፍቅር መንገድን ተቀብለው ወደሰላም እንዲመጡ ተጠየቀ

71
ጅግጅጋ ሀምሌ 4/2010 የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) አመራሮች ዶክተር አብይ አህመድ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ባቀረቡት የይቅርታና የፍቅር መንገድ ወደ ሰላም እንዲመጡ የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳደር አቶ አብዲ መሀሙድ አስታወቁ። የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሀሙድ ኡመር ይህንን ያሉት ዛሬ በተጀመረው የክልል ምክር ቤቱ ሰባተኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት አንድ መቶ ቀናት ያስመዘገቡትን ስኬት ለምክር ቤቱ አባላት ባብራሩበት ወቅት ነው፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት በኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ደረጃ የጠቅላይ ሚኒስቴሩን የይቅርታ፣ የፍቅርና የመደመር መርህ ከግብ ለማድረስ የበኩላቸውን ለመወጣት በስፋት ውይይት ተደርጓል፡፡ "በዚህም የክልሉ መንግስትና ገዥው ፓርቲ ኢሶዴፓ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ላከናወኗቸው ሥራዎች ትልቅ ክብር አለን፤ መደመርን መርጠናል" ብለዋል አቶ አብዲ። ቀደም ሲል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ተፈርጆ የነበረው ኦብነግ ከመንግስት የተሰጠውን እድል በመጠቀም ወደሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገባም ጠይቀዋል። በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን የይቅርታና የፍቅር መንገድ ጥሪ የግንባሩ መሪዎች አክብረው በመቀበል እድሉን እንዲጠቀምበት ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡ የግንባሩ አመራሮች ለዓመታት የያዙትን ጥላቻ በማስወገድ ለቀረበላቸው የሰላም ጥሪ አዎንታዊ  ምላሽ በመስጠት በአገሪቱና በክልሉ የተጀመሩ የፍቅር፣ የአንድነትና የመደመር መርህ አካል እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳደሩ በምክር ቤት ንግግራቸው አክለው እንደገለጹት የክልሉ መንግስትና መሪ ድርጅቱ የህዝቡን ሰላም ለማረጋገጥና የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል አበክረው ይሰራሉ። ቀደም ሲል በህዝቡ ላይ ለተፈፀሙ ስህተቶች የክልሉ መንግስትና መሪ ድርጅቱ ኃላፊነት እንደሚወስዱ ገልፀው ህዝቡን በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ " ሥራ ሲሰራ ስህተቶች ይኖራሉ፤ ነገር ግን በጎ ተግባራትን ማጎልበት እንዲሁም ለተፈጠሩ ስህተቶች በይፋ ይቅርታ መጠየቅ መልካም ባህል በመሆኑ ሁላችንም ማዳበር ይኖርብናል’’ ብለዋል፡፡ የክልል ምክር ቤቱ ጉባኤ በነገው እለትም ቀጥሎ እንደሚውል ታውቋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም