የሴቶች ሊግ አባላት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የቦንድ ግዥ አከናወኑ

60

ደብረ ብርሃን ነሐሴ 8/2012 (ኢዜአ) በብልጽግና ፓርቲ የደብረ ብርሃን ከተማ ሴቶች ሊግ አባላት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድጋፍ የሚውል ከ111 ሺህ 800 ብር በላይ የቦንድ ግዥ አከናወኑ።

በደብረ ብርሃን የብልፅግና ሴቶች ሊግ አዘጋጅነት "ደሜን ለወገኔ ድምፄን ለግድቤ " በሚል መሪ ሀሳብ  የቦንድ ግዥና  ደም ልገሳ መረሃ ግብር  ተካሄዷል።

የከተማው ሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ   ወይዘሮ ሽብሬ ዓለሙ በመረሃ ግብሩ ስነ-ስርዓት እንደገለጹት  በበጀት ዓመቱ  ከአባላት ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማሰባሰብ ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።

ቀደም ሲልም  ሴቶች ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ ለቀሪውም ስራ የድርሻቸውን ለመወጣት  በቦንድ ግዥ እየተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በትናንቱ ስነ-ስርዓት አንድ ሺህ 43 ሴቶችን በማሳተፍ 111 ሺህ 860 ብር የቦንድ ግዥ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ማከናወናቸውን አስታውቀዋል።  

የሊጉ አባላት  እስከ  10 ሺህ ብር ድረስ የቦንድ ግዥ በመፈፀም ተሳትፈዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ እታፈራሁ ተሰማ  በበኩላቸው   ግድቡ  ውሃ መያዙ ይፋ ከሆነበት ዕለት  ጀምሮ የከተማው ነዋሪዎች በመነሳሳት በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር  ላይ  በመሳተፍ ድጋፋቸውን መግለጻቸውን ተናግረዋል።

የከተማው አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ መርከብ ለማ እንዳሉት ሃገር የሚለማውና የሚያድገው መንግስትና ህዝብ ተደጋግፈው ሲሰሩ ብቻ ነው።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ አሁን ወደ ከተማዋ የሚመጣውን የቱሪስት እና የኢንቨስትመንት ፍሰት ይበልጥ  ለማሳደግ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸው ነዋሪዎች ለግድቡ ግንባታ ድጋፋቸውን  እንዲቀጥሉም  መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በከተማው የቀበሌ ሶስት ነዋሪ  ወይዘሮ መሰረት ተክሌ  በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል ለግድቡ ግንባታ  ከሰባት ሺህ ብር በላይ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አስታውሰው ፤ ትናንት ደግሞ የአንድ ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም