በትግራይ የአሸንዳ በዓልን ልጃገረዶች ሲያከብሩ እራሳቸውን ከኮሮና በመጠበቅ ሊሆን ይገባል-- ግብረ ኃይሉ

62

መቀሌ ነሐሴ 8/2012 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል በየዓመቱ ከነሐሴ 16 ቀን ጀምሮ ለሳምንታት የሚቆየው የአሸንዳ በዓል ልጃገረዶች ሲያከብሩ እራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ ሊሆን እንደሚገባ የክልሉ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አሳሰበ።

አሸንዳ ልጃገረዶች በዓመት አንድ ጊዜ በጋራና በነጻነት ባህላቸውን የሚገልጹበት በዓል ሆኖ ሲከበር የቆየ ነው።

በግብረ ኃይሉ  የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢና የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሐጎስ ጎዲፋይ እንደገለጹት በልጃገረዶች ዘንድ ተወዳጅ የሆነውን ይሄው በዓል  በቫይረሱ ምክንያት ዘንድሮ በአደባባይ እንዳይከበር በግብረ ኃይሉ ተወስኗል።

በዓሉ በተለመደው ሁኔታ  ልጃገረዶች ተሰብስበው ማክበር ለኮሮና ቫይረስ መዛመት አደገኛ በመሆኑ እራሳቸውን በመጠበቅ  ቤታቸው ማክበር እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ልጃገረዶች  በጎዳናዎች ላይ በመውጣትና  በየአደባባዩ በመሰብሰብ የሚያሳዩት ባህላዊ ትርኢትና ፌስቲቫል በወረርሽኙ  ምክንያት ዘንድሮ አይኖርም ብለዋል።

በየዓመቱ  ከነሐሴ 16 ቀን ጀምሮ  ለሳምንታት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በስፋት ይከበር የነበረው    በበሽታው  ምክንያት በጋራ ለማክበር አስቸጋሪ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ሴቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር የትምወርቅ ገብረመስቀል ናቸው።

ይህንን አስቸጋሪ ሁኔታ በመረዳት ልጃገረዶች በዓሉን ሲያከብሩ በሽታውን ለመከላከል የወጣውን መመሪያ በመተግበር ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአሸንዳ በዓል ልጃገረዶች በየዓመቱ  በጋራና በነጻነት ባህላቸውን የሚገልጹበት በዓል ቢሆንም   የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ በመጠቀምም ለማክበር አስቸጋሪ በመሆኑ የግብረ ኃይሉ ውሳኔ መከበር እንዳለበት አሳስበዋል።

በዓሉ " ኮሮና ለመከላከል አሸንዳ በቤታችን"  በሚል መሪ ሀሳብ ልጃገረዶች እራሳቸውን በመጠበቅ በቤታቸው ሆነው እንዲያከብሩም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም