በትግራይና አፋር አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው

54

ማይጨው ነሐሴ 6 ቀን 2012(ኢዜአ) በትግራይ ደቡባዊ እና በአፋር ዞን ሁለት አዋሳኝ አካባቢዎች ዳግም የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።

በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተገልጿል።

በትግራይ ደቡባዊ ዞን ግብርናና ገጠር ልማት መመሪያ  የአዝርት ባለሙያ አቶ ክብሮም በርሄ ለኢዜአ እንደገለጹት ከተያዘው ሳምንት መግቢያ ጀምሮ በአዋሳኝ ቦታዎች ላይ የአንበጣ መንጋ ዳግም ተከስቷል ።

በአዋሳኝ አካባቢዎች ለአንበጣ መንጋ መራቢያ አመቺ ቦታዎች መኖራቸውም ተረጋግጦ  በጋራ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ጥረቱም መንጋውን የሚረብሽ ድምፅ በማሰማት ማባረር ዘላቂ መፍትሔ ስለማይሰጥ በኬሚካል ርጭት  የታገዘ የመከላከል ስራ  መሆኑን አስረድተዋል።

መንጋውን የሚከታተሉ ባለሙያዎች ከመመደብ በተጨማሪ ሁለት ሺህ ሊትር ኬሚካል ወደ ስፍራው መላኩን ገልጸዋል።

"ከአካባቢው አርሶአደሮች ጋር በመነጋገር አንበጣው ባረፈባቸው አካባቢዎች ኬሚካል ለመርጨት በቅንጅት እየሰራን ነው" ብለዋል ።

በአፋር ክልል ዞን ሁለት የመጋሌ ወረዳ የግብርናና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሑሩይ ዳውድ በበኩላቸው በወረዳው በተያዘው ሳምንት  የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በአዝርእት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለሙያዎችን በማስማራት መንጋው ያረፈበትን ቦታ በመለየት የኬሚካል ርጭት ለማካሄድ ጥረት እየተደረገ ነው።

ከተጎራባቹ ትግራይ ክልል ጋር  መረጃ በመለዋወጥና በመተባበር የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን አቶ ሑሩይ ገልጸዋል።

በትግራይ ደቡባዊ ዞን ራያ አዘቦ ወረዳ የገነቴ ቀበሌ አርሶ አደር ተክለብርሃን ጀምበሬ የአንበጣ መንጋው በአንድ ሄክታር ማሳቸው ላይ የሚገኝ የማሽላ ቡቃያ ላይ  ጉዳት እንዳያደርስ ክትትል እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

''ባለፈው ዓመት በቀበሌያችን የአንበጣ መንጋው በተደጋጋሚ ተከስቶ በአዝርእት ላይ ጉዳት ሳያደርስ መከላከል ችለናል" ያሉት ደግሞ የዚሁ ቀበሌ  አርሶአደር አብርሃ ታረቀ ናቸው።

ዳግም የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል እየተዘጋጁ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም