የኮሮና መከላከያ መልዕክቶች የየዕለት መግባቢያ ቋንቋችን ሊሆኑ ይገባል... አርቲስት ጥላሁን ጉግሳ

147

ነሀሴ 8/2012(ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስን  በተመለከተ የሚተላለፉ  የጥንቃቄ መልዕክቶችን  ህብረተሰቡ የየእለት መግባቢያ ቋንቋው አድረጎ ሊጠቀምበት እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረገው የፊልምና የቲያትር ባለሙያ አርቲስት ጥላሁን ጉግሳ  እንደገለጸው  በኮሮና ላይ ያሳየነው መዘናጋት ሩቅ መስሎ  ይታይ የነበረውን ችግር  ወደ እያንዳዳችን ቤት እንዲገባ አድርጎታል፡፡

በአንድ የቁጥር አሀዝ የታየው የኮሮና ተጠቂዎች ቁጠር ከሁለት ወደ ሶስት አሁን ደግሞ  ወደ አራት አሃዝ  ከፍ ብሏል ያለው አርቲስቱ፤  “ይህም  በሽታው በተከሰተበት  ጊዜ  የነበሩ  የጥንቃቄ ተግባራት እየተቀዛቀዙ በመምጣታቸው ነው” ብሏል፡፡

እንደ አርቲስት ጥላሁን ገለጻ የቅድመ መከላከል ተግባራቱ ቀላልና ማንኛውም  ሰው  ሊከውናቸው  የሚቻሉ ሆነው ሳሉ በዚህ ረገድ የሚታየው  መዘናጋት  ግን  ጉዳቱን  እያባባሰው  መጥቷል፡፡

ለአብነትም በበሽታው የሚያዙ ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመምጣቱም በላይ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች መካከል 80  በመቶ  የሚሆኑት  ምልክት  አለማሳየታቸው  የበሽታውን  መስፋፋት  አስከፊ  አድርጎታል፡፡

ችግሩን ለመቀነስ በመገናኛ ብዙኃንና በሌሎች መንገዶች የሚተላለፉ የቅድመ  መከላከል  የጥንቃቄ  መልዕክቶች የህብረተሰቡ የየዕለት  መግባቢያ  ቋንቋ  ከመሆን አልፈው  “እንደ ብሔራዊ መዝሙር  ሁሉም  ውስጥ  እስኪሰርጽ  ድረስ ማስተማር  ይገባል” ነው  ያለው፡፡

የኪነጥበብ ባለሙያዎች በሚያዘጋጇቸው ኪነጥበባዊ ስራዎችም በሽታውን ለመከላከል  መወሰድ የሚገባቸውን  የጥንቃቄ መልእክቶች በተመለከተ  ትኩረት ሰጥተው  ሊሰሩ  እንደሚገባ አስረድቷል፡፡

በሲትኮም ድራማ ታሪክ በኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ በታየው ቤቶች ድራማ  ኮቪድ-19ን  የተመለከቱ ከሦስት በላይ ክፍሎች መተላለፈቸውንና አሁንም በድራማዎቹ ውስጥ ኮሮናን የሚመለከቱ መልዕክቶች እንደሚተላለፍበት  በምሳሌነት አንስቷል፡፡

በሽታው የሁሉንም ደጅ ያንኳኳ እንደመሆኑ የኪነጥበብ ባለሙያውም በጥበባዊ መንገድ  ቫይረሱን የተመለከቱ የጥንቃቄ መንገዶችና መረጃዎችን ማስተላለፍ እንደሚኖርበት  ጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል ከኪነጥበብ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን በአዲስ አበባ የተለያዩ አደባባዮች  የግንዛቤ  መስጨበጫ መርሐ-ግብሮችን  ማከናወናቸውንና  በኮሮና ለተጎዱት  ደግሞ  ድጋፎች ማሰባሰባቸውን አስታውሷል፡፡

የተሰበሰበውን ድጋፍ  ለከተማ አስተዳደሩ ማስረከባቸውንና በቀጣይም  በተለያዩ  ክልሎች  ግንዛቤ ለመስጠትና ድጋፍ ለማሰባሰብ እንቅስቃሴ እያደረጉ  መሆኑን  ተናግሯል፡፡

አብሮ የመብላት ልምድ እንዳለን ሁሉ ከአጥራችን ወጥተን ያለንን  በማጋራት ኮሮና  እያደረሰ ያለውን ጉዳት  ልናልፈው ይገባል  ሲል መልዕክቱን  አስተላልፏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም