በእነ አቶ ጃዋር መሃመድ መዝገብ 5 ተጠርጣሪዎች ባለመቅረባቸው የቀዳሚ ምርመራ ምስክሮች ሳይሰሙ ቀረ

49

አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 07/2012 ( ኢዜአ) በወንጀል ጉዳይ በተጠረጠሩት እነ አቶ ጃዋር መሃመድ መዝገብ 5 ተጠርጣሪዎች ባለመቅረባቸው የቀዳሚ ምርመራ ምስክሮች ሳይሰሙ ቀረ።

በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የአራዳ ተረኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ጉዳያቸው ታይቷል።

መገናኛ ብዙሃን ችሎቱን በፕላዝማ ቴሌቪዥን እንዲከታተሉ በሌላ አዳራሽ ተገኝተው የነበረ ቢሆንም የፕላዝማ ቴሌቪዥኑ ድምጽ መሰማት ባለመቻሉ መከታተል ሳይችሉ ቀርተዋል።

ሆኖም ከችሎት በኋላ ከዐቃቤ ህግ እና ከተጠርጣሪ ጠበቆች የእለቱን የችሎት ሁኔታ የሚገልጽ መረጃ ማግኘት ተችሏል።

ችሎቱ አቶ ጃዋር መሃመድን ጨምሮ በ14 ተጠርጣሪዎች ላይ የቀዳሚ ምርመራ ምስክሮችን ቃል ለመስማት ተሰይሞ የነበረ ቢሆንም 4ኛ፣ ከ6ኛ እስከ 9ኛ ያሉት ተጠርጣሪዎች በኮሮናቫይረስ በመጠርጠራቸው ሳቢያ ሳይቀርቡ ቀርተዋል።

አጃቢ ፖሊስ ያልቀረቡበትን ምክንያት ተጠይቆ በሰጠው ማብራሪያ ያልቀረቡት በኮሮናቫይረስ በመጠርጠራቸው ምክንያት መሆኑን አስረድቷል።

ሶስት ምስክሮችን ለማሰማት ቀርቦ የነበረው ዐቃቢ ሕግ በቀረቡት ተጠርጣሪዎች ላይ ምስክሮች እንዲሰሙለት ጠይቆ ነበር።

5ቱ በኮሮናቫይረስ የተጠረጠሩት ጤንነታቸው ተረጋግጦ መቅረብ እስኪችሉ ድረስ ባሉት ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ላይ ምስክር ይሰማልኝ ሲል ጠይቋል።

ማስረጃ የሚያቆይ ችሎት ስለሆነ መቀጠል ይችላል ሲልም ነው አቃቢ ህግ ያስረዳው።

የተጠርጣሪዎች ጠበቆች የፍርድ ቤቱ ቀጠሮ እንዲስተካከል፣ የተጠርጣሪዎች ቤተሰቦች የባንክ ሂሳብ ቁጥር እንዲከፈትና በተጠርጣሪዎች አያያዝ ላይ ችግር እንዳለ በመግለጽ አቤቱታ አቅርበዋል።

አቶ ጃዋር በበኩላቸው ከእሳቸው ጋር የተያዙት የግል ጠባቂዎቻቸው በእሳቸው የተነሳ መቀጣት እንደሌለባቸው በመግለጽ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል።

አቶ ሃምዛ አዳነ የተባሉት ተጠርጣሪም ውክልና ለመስጠት ሄደው ከፖሊስ ደብዳቤ መጻፍ አለበት በሚል እንዳልተስተናገዱ ገልጸው አቤቱታ አቅርበዋል።

ዐቃቤ ሕግ ቀጠሮን በተመለከተ በቀረበው አቤቱታ ላይ በሰጠው አስተያየት ፍትህ መፋጠን ስላለበት ቶሎ ቶሎ ቀጠሮ መሰጠቱ ትክክል እንደሆነ ገልጿል።

ዐቃቤ ሕግ የሚሰጠውን ቀጠሮ የሚሰማው ከፍርድ ቤቱ እንደሆነ ተናግሯል።

ግራ ቀኙን ያደመጠው ችሎቱ በሰጠው ትዕዛዝ ቀጠሮ ቶሎ ቶሎ የሚሰጠው ተገቢነት ስላለው እንደሆነ አብራርቷል።

ፌዴራል ፖሊስ የተጠርጣዎች አያያዝን በተመለከተ ቀርቦ እንዲያስረዳ ታዟል።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና የሁሉንም ተጠርጣሪዎች የኮሮናቫይረስ የምርመራ ውጤት እንዲያቀርብ በማዘዝ የዐቃቤ ህግ የቀዳሚ ምርመራ ምስክሮችን ለመስማት ለሰኞ ነሐሴ 11 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም