በአፍሪካ በስራ እድል ፈጠራና ገቢ ተመጣጣኝነት ክፍተት ይታያል

77
አዲስ አበባሀምሌ 4/2010 የአፍሪካ ምጣኔ ሀብት ዓመታዊ ምጣኔ እያደገ ቢሆንም በስራ እድል ፈጠራና ገቢ ተመጣጣኝነት ረገድ ያለው ክፍተት ማሻቀቡን አንድ ጥናት አመለከተ። የአፍሪካ ሕብረት ኢኮኖሚክ ጉዳዮች ኮሚሽን ‘ኦ ኢ ሲ ዲ' ከተሰኘ አንድ ኢኮኖሚክ ትብብርና ልማት ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር በመተባበር ያስጠናው በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የአፍሪካን ምጣኔ ሀብት ዕድገት የሚዳስስ የጥናት ሰነድ ዛሬ ይፋ ተደርጓል። በጥናቱ መሰረትም አፍሪካ ከአውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር ከ2000 በኋላ በየዓመቱ የሚመዘገበው የምጣኔ ሀብት ምጣኔ ከእስያ ቀጥሎ በዓለም ላይ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። እድገቱ ከ1990ዎቹ በነብስ ወከፍ ገቢ ስሌት ከዜሮ በታች የነበረው ምጣኔ ሀብታዊ እድገት፤ እ.አ.አ ከ2000 እስከ 2008 በነፍስ ወከፍ ገቢ በሶስት ነጥብ አንድ በመቶ ሲያድግ ዓመታዊ ዕድገቱም አምስት ነጥብ አምስት በመቶ እንደሆነ ተመልክቷል። የበርካታ የአፍሪካ አገሮች ዓመታዊ ዕድገት በተከታታይ ዓመታት ማደጉን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ አፍሪካ ከ2000 እስከ 2017 ባሉት ተከታታይ ዓመታት በአማካይ በየዓመቱ አራት ነጥብ ስድስት በመቶ አድጋለች። በዚህም አፍሪካ ከቻይና፣ ህንድና ሌሎች በእድገት ላይ ከሚገኙ አጋሮቿ ጋር የፈጠረችው የገቢና ወጭ ንግድ ትስስር በ2000 ከነበረው 276 ቢሊየን ዶላር በ2016 መጨረሻ ወደ 806 ቢሊየን ዶላር አድጓል። በአህጉሪቷ ለተመዘገበው ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት የምርቶች ዋጋ መሻሻል፣ የተሻሻሉ አጠቃላይ ምጣኔ ሀብታዊ አስተዳድርና ስትራቴጂዎች እንዲሁም እርዳታ ብድር አቅርቦት መልካም አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ነው የተመለከተው። ያም ሆኖ ግን አፍሪካ ያስመዘገበችው ዓመታዊ እድገት ምጣኔ ቢያድግም በዜጎች ስራ ዕድል ፈጠራና በገቢ ተመጣጣኝነቱ ረገድ ያለው ክፍተት በዚያው ልክ እያሻቀበ ነው። ለአብነትም እ.አ.አ በ2063 አጀንዳ በስራ ዕድል ፈጠራ ረገድ በ2023 በቂ ስራ ያልተፈጠረላቸው አፍሪካውያንን ቁጥር ወደ 41 በመቶ ለመቀነስ ቢታቀድም፤ አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለ ግን እ.አ.አ በ2022 በቂ ስራ ያልተፈጠረላቸውን ዜጎች ቁጥር ከ66 በመቶ መቀነስ አይቻልም። በአፍሪካ ሕዝብ መካከል ያለው የገቢ ልዩነት ወይንም በጠቅላላ ሃብት ስርጭት መጠን መለኪያ ስሌት 41 ነጥብ ሲሆን፤ ይህም በእስያ ካለው 35 ነጥብ ከፍ ያለ ነው። በድህነት መጠን ረገድ ደግሞ እጅግ በአስከፊ ድህነት ውስጥ የነበሩ ዜጎች ቁጥርን በ1990 ከነበረበት 45 በመቶ በ2013 ወደ 35 በመቶ መቀነስ ቢቻልም፣ በተመሳሳይ በቀን አንድ ነጥብ ዘጠኝ ዶላር በታች ገቢ ያላቸው ዜጎች ቁጥር ከ280 ሚሊየን ወደ 395 ሚሊየን አሻቅቧል። በኢኮኖሚያዊ ትብብርና ልማት ዓለም አቀፍ ድርጅት ዳይሬክተር ማሪዎ ፔዚኒ አፍሪካ እ.አ.አ በ2063 ለያዘቻቸው አጀንዳዎች ስኬትና ለዘላቂ አህጉራዊ ምጣኔ ሀብት ዕድገት ብዙ ስራ ይጠይቃል። ስለሆነም የድህነትን መጠን ለመቀነስ፣ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ፣ የምርትና ምርታማነት ለማሻሻል አህጉራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ለዚህ ደግሞ በየወቅቱ የሚሻሻሉ ፖሊሲዎች እንደሚያስፈልጉ ነው ያብራሩት። የአፍሪካ ሕብረት ኢኮኖሚክ ጉዳዮች ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ቪክቶር ሐሪሰን፤ የአፍሪካ ሕብረት ጥናቱ አህጉሪቷ በ2063 አጀንዳ ለያዘቻቸው ግቦች ስኬት ከወዲሁ አበክሮ ለመስራት የሚያስችል ግንዛቤ የሚፈጥር እንደሆነ ተናግረዋል። ከዚህ ባለፈ አገራቱ ከሌሎች አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ሁሉን አቀፍ ትስስር በመፍጠር አካታችና ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እድገት እንዲያመጡ የሚስችሉ ፖሊሲዎችን እንዲቀርጹም በግብዓት እንደሚያገለግል ነው ያነሱት። አገራቱ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ የምርት አይነቶችን፣ በጥሬ ምርቶች ላይ እሴት መጨመርና ይህን የሚደግፍ አገራዊ ፖሊሲ ማውጣትና መተግበር እንደሚያስፈልግ ሪፖርቱ አመልክቷል። አፍሪካ ያላት የመልማትና የማደግ አቅም በአግባቡ ከተመራ የወደፊት ተስፋዋ የለመለመ እንደሆነ ተጠቅሷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በዛሬው ዕለት የተሻሻለው የአፍሪካ ተስማሚነት ያለው መረጃ ስትራቴጂ ሰነድም ይፋ ሆኗል። በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን ተጠንቶ የተዘጋጀው የመረጃ ስትራቴጂ ሰነዱ አፍሪካ በ2063 ለያዘችው ዘላቂ ግብ ስኬት ለፖሊሲ ግብዓት የሚውሉ ታማኒነት ያላቸው አህጉር አቀፍ መረጃዎች እንዲወጡ ያለመ ነው ተብሏል። በአፍሪካ የሚወጡ ፓለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ መስኮች የሚወጡ መረጃዎች ምድር ላይ ካለው እውነታ ጋር የሚጣረሱ መረጃዎችን በማስወገድ በቀጣይ በሁሉም መስኮች ወቅታዊ፣ ታማኒና ተስማሚ አህጉራዊ መረጃዎችን ለመሰብሰብ እንደሚያስችል በመድረኩ ላይ ተመልክቷል። ይህም የሕብረቱ አባል አገሮች መሪዎች በፓለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ መስኮች ቅንጅት እንዲፈጥሩና በአህጉራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጥራት ያለው መረጃ ስርዓት እንዲዘረጋ እንደሚያደርግ ነው የተገለጸው።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም