በኢትዮጵያ ዘመናዊ የክትትልና ግምገማ ስርዓት በዛሬው እለት ይፋ ተደርጓል

82

አዲስ አበባ፣ነሐሴ 7/2012 (ኢዜአ) ዘመናዊ የክትትልና ግምገማ ስርዓቱ በኢትዮጵያ የተጀመረውን ሪፎርምና የኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤታማ እንዲሆን ጉልህ ሚና እንዳለው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለፁ።

የፕላንና ልማት ኮሚሽን ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ዲጂታል የክትትል እና ግምገማ ሥርዓት በይፋ ተጀምሯል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ ሌሎች ሚኒስትሮች ተገኝተው በይፋ አስጀምረውታል።

ይህ ዘመናዊ ስርዓት የ10 ዓመቱን መሪ የልማት ዕቅድ ጨምሮ የተለያዩ የልማት እቅዶችንና ፕሮጀክቶችን አፈፃፀም ውጤታማነት ለማገዝ እንዲያስችል ተደርጎ አገራዊ ሁኔታዎችን በማገናዘብና በአገር ውስጥ ባለሙያዎች የተዘጋጀ ስለመሆኑ ተገልጿል።

ዲጂታል መተግበሪያው ተጠያቂነት ያለበት አገራዊ የክትትልና ግምገማ ስርዓት መገንባት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት የተዘጋጀ መሆኑም ተነግሯል።

በማስጀመሪያ ስነስርዓቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለውጡን በውጤታማነት ለመምራት የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ በየሴክተር መስሪያ ቤቱ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱን አውስተዋል።

በመሆኑም የልማት እቅዱን በትክክል ለመምራት ዘመናዊ የክትትልና ግምገማ ስርዓት ጠቃሚ መሆኑን ገልፀዋል።

የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ፍፁም አሰፋ እንደተናገሩት ቴክኖሎጂው የልማት እቅዶች በታቀደላቸው ጊዜ፣ ወጪ እና ጥራት እንዲከወኑ ያስችላል።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዶክተር አብርሃም በላይም የቴክኖሎጂውን አስፈላጊነት አብራርተዋል።

ለልማት እቅዶች ስኬትና መፋጠን ከፍተኛ አስተዋጾ እንዳለውም አስረድተዋል።

የልማት እቅዶችና ፕሮጀክቶችን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ለመከታተልና ለመገምገም እንዲሁም አስፈላጊውን ውስኔ ለመስጠት የሚያግዝ ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ተቋማቶችን የሚመሩ ሚኒስትሮች ደግሞ ዘመናዊ የክትትልና ግምገማ ስርዓቱ በየዘርፋቸው

ሊያስገኝ የሚችለውን ጠቀሜታ በማስመልከት ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል።

በአስተያየታቸውም ቀጣዩን የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመምራት አስተዋፆኦ እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።

የክትትልና የግምገማ ስርዓቱ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆንና ከሂደት ይልቅ ስኬት እና ውጤት ላይ እንዲያተኩር ተደርጎ የተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በ10 ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የየዘርፋቸውን ቀጣይ የ10 ዓመት ዕቅድ በማቅረብ በባለሙያዎች እንዲተች እና ህብረተሰቡም ጥያቄና አስተያየት ሲሰጥበት ቆይቷል።

መሪ የልማት እቅዱ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት መሆኗን የሚያረጋግጥ እንደሚሆን ታምኖበታል።

የፕላንና ልማት ኮሚሽን እና የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በቀጣይ በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም