የአፋር ክልል ምክር ቤት ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አጸደቀ

77

ሰመራ ነሐሴ 7/2012(ኢዜአ) የአፋር ብሄራዊ ከልላዊ መንግስት ምክር ቤት አምስኛ ዓመት የስራ ዘመን አስረኛ መደበኛ ጉባኤ ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ ለ2013 በጀትና የተለያዩ ሹመቶችን አጸደቀ። 

የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ ሃሰን የክልሉን የ2012 ዓም የስራ አፈጻጸምና ተያያዥ ወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረግ በጀቱ መዘጋጀቱን ተናግረዋል ።

"በጀቱ ከ2012 በጀትአመት ጋር ሲነጻጸር በአንድ ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው" ብለዋል ።

የበጀት ምንጩም ከፌዴራል መንግስት ግምጃ ቤት፣ ክልሉ ገቢ፣ ከውጭ እርዳታ የሚሸፈን መሆኑን አብራርተዋል ።

በጀቱ በዋናነት በክልሉ የድርቅ ተጋላጭነት ለሚቀንሱ የማህበራዊና የኢኮኖሚ መሰረተ-ልማቶች  ማስፋፋትና ለልማት ስራዎች ማኪያሄጃ የሚውል መሆኑን  አመልክተዋል ።

በክልሉ በ2013 በጀት ዓመት ለተለያዩ የልማት ስራዎች ማስፈጻሚያ በቀረበው ረቂቅ በጀት ላይ ውይይት ተደርጎ በምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ፀድቋል ።

የምክር ቤቱ አባላት በጀቱ ከብክነት በጸዳ መልኩ የህብረተሰቡን ችግር ለሚፈቱ ስራዎች አግባብ ባለው መልኩ እንዲውል አሳስበዋል ።

የክልሉ ርዕሰ-መስዳድር አቶ አወል አርባ ወቅታዊ ሀገራዊ የለውጥ ጅምሮችን ጫፍ ለማድረስ የተሻለ ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት ያላቸው አመራሮች ክፍተት በታየባቸው ቦታዎች የአስፈጻሚ አካላት መተካትና ሸግሽግ ማካሄድ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ለምክር ቤቱ ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ በርዕሰ መሰተዳድሩ የቀረበውን የካቢኔ ሹመት በአብላጫ ድምጽ አድቋዋል።

በዚህም መሰረት፣

 1ኛ አቶ ኢለማ አቡበከር የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድርና ውሃ ሃብት ቢሮ ኃላፊ

 2ኛ አቶ መሃመድ ጠይብ  የጤና ቢሮ ኃላፊ

3ኛ አህመድ መሃመድ ቦዳ  የትምህርት ቢሮ

4ኛ አቶ ጠሐ አህመድ የመንግድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ

5ኛ አቶ ኢብራሂም ሁመድ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ

6ኛ አቶ  መሀመድ ኡዳ  የገጠር መሬት አስተዳደርና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ

7ኛ አቶ መሃመድ አሊ  የኪል በቲ-ረሱ ዞን ዋና አስተዳዳሪ

8ኛ አህመድ ኢብራሂም የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል።

ዛሬ ማምሻውን እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀው የምክር ቤቱ   ጉባኤ የዞን ዳኞችን ሹመትና አዋጆችን እንደሚያጸድቅ ለጉባኤው ከወጣው መርሀ ግብሩ ማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም