ከመስኖ ልማት በሚያገኙት ገቢ ኑሮቸው እየተለወጠ መሆኑን በድሬዳዋ አርሶ አዴሮች ገለጹ

54

ድሬዳዋ ነሐሴ 7 ቀን 2012 (ኢዜአ) - በአካባቢያቸው በተመቻቸላቸው የመስኖ ፕሮጀክት የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት በሚያገኙት ገቢ ኑሮቸው እየተለወጠ መሆኑን በድሬዳዋ አሰተዳደር የገጠር ቀበሌዎችአስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አርሶ አደሮች ገለጹ።

በአስተዳደሩ  የዱጁማ ገጠር ቀበሌ  አርሶአደር አደም መሐመድ እንዳሉት  ባለፉት አምስት ዓመታት በተሰማሩበት የመስኖ ልማት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።

"ባለችኝ አነስተኛ መሬት ላይ ከማለውን ቲማቲም፣ሽንኩርትና ቃሪያ በመሸጥ በዓመት ከወጭ ቀሪ 30 ሺህ ብር አገኛለሁ" በዚህም በሴፍቲ ኔት ከሚደረግልኝ እርዳታ በመውጣት  እራሴን ችያለሁ ብለዋል፡፡ 

ከሚያመርቱት የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ሽያጭ በዓመት ከ50 ሺህ ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ በማፍራት ተጠቃሚ እንደሆኑ የገለፁት የዋሂል ቀበሌ  አርሶ አደር ሙሜ አብዱረህማን "ልጆቼን በሙሉ አስተምራለሁ፤ ሱቅ ከፍቼ ተጨማሪ ገቢ እያገኘሁ ነው" ብለዋል፡፡


ወይዘሮ መይሙና ኢብራሂም በበኩላቸው ቀደም ሲል እርዳታ ጠባቂ እንደነበሩ አስታውሰው  ፡"ከባለቤቴ ጋር በመስኖ የምናመርተውን የጓሮ አትክልት በከተማ ባቋቋምነው መደብር ለሽያጭ እያቀረብን ነው" ብለዋል።

ወይዘሮ መይሙና " ከ150 ሺህ ብር በላይ  ባንክ አለኝ፤ የኔን ፈለግ እንዲከተሉ በርካታ ሴቶችን አንቅቻለሁ"ብለዋል፡፡

የኮሪሶ ቀበሌ አርሶአደር ሙክታር ኢድሪስ በበኩላቸው ከከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የሚኖሩ በመሆናቸው በመስኖ የሚያመርቱትን የጓሮ አትክልት በቀላሉ ለገበያ ለማቅረብ የረዳቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ እንደገለጹት በገጠር ቀበሌዎች በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የመስኖና አማራጭ የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው በመተግበር ላይ ናቸው፡፡

"በሁለተኛው የዕድገትና የትራስፎርሜሽን ዕቅድ ጅማሮ 3ሺህ 200 ሄክታር የነበረው በመስኖ የሚለማ መሬት አሁን ላይ ወደ 4ሺህ 200 ሄክታር ከፍ ብሏል" ብለዋል ።

 ከመስኖ የሚገኘው የምርት መጠንም  ከ430 ሺህ  ኩንታል ወደ 1 ሚሊዮን 100 ሺህ ኩንታል ማደጉን ጠቅሰዋል ።

የመስኖ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ቁጥርም ከ9ሺህ 600 ወደ 13ሺህ 200  መድረሱን ተናግረዋል።

እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ በተያዘው በጀት ዓመት የመስኖ ልማት ተጠቃሚዎችን ቁጥር የማሳደግ፣ ልማቱን የማስፋፋትና አማራጭ የገቢ ማግኛ ፕሮጀክቶችን የማጠናከር ሥራ የትኩረት አቅጣጫ ነው።

 በድሬዳዋ አስተዳደር ገጠር ቀበሌዎች 64 ሺህ ነዋሪዎች  በሰፍትኔት  የታቀፉ መሆናቸው ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም