አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለጅቡቲው ፕሬዝዳንት አቀረቡ

95

አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 7/2012 (ኢዜአ)አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለጅቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ አቀረቡ።

በጀቡቲ የኢፌዲሪ ባለሙሉስልጣን አምባሳደር በመሆን በቅርቡ የተሾሙት ብርሃኑ ጸጋዬ ለጅቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ የሹመት ደብዳቤያቸውን አቅርበዋል።

አምባሳደር ብርሃኑ በቆይታቸው የሁለቱን አገራት ህዝቦች የቆየ ወዳጅነት እና ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ የሹመት ደብዳቤያቸውን ባቀረቡበት ወቅት ተናገረዋል።

ከጅቡቲ መንግስትና ህዝብ ጋር በቅርበት ውጤታማ ስራ ለማከናወን ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የጅቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ በበኩላቸው የአገራቸው መንግስት የሁሉቱን አገራት ሁሉን አቀፍ ግንኙነትና ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል።

የኢትዮጵያና የጅቡቲ የመንግስት ለመንግስት እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለዘመናት የዘለቀና በሁሉም መስክ በምሳሌነት የሚገለጽ መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

ለአምባሳደር ብርሃኑ ስራ ስኬት መንግስታቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ማረጋገጣቸውን የኢፌዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።

አምባሳደሩ በቆይታቸው የሁሉቱን አገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰሩም ፅኑ እምነት አለኝ ብለዋል ፕሬዝዳንት ጌሌ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም