የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮሮና ያደርሳል ተብሎ ከተተነበየው አስከፊ ጉዳት ታድጎናል ...ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ

64

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2012(ኢዜአ) "የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የኮሮና ቫይረስ ያደርሳል ተብሎ ከተተነበየው አስከፊ ጉዳት ታድጎናል" ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

የአስቸካይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጻም መርማሪ ቦርድ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለተቋቋመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ የመስክ ምልከታ ግብረ መልስ አቅርቧል።

የቦርዱ አባላት በኦሮሚያ፣ አማራና የደቡብ ብሔር፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች በማቅናት ነው የመስክ ምልከታውን ያከናወኑት።

አባላቱ እንዳሉት በዝግጅት ምዕራፍ በተከናወኑ ተግባራት በተለይ ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችሉ አደረጃጃቶችን በአጭር ጊዜ በማቋቋም ረገድ ጠንካራ ስራ ተሰርቷል።

የምርመራ አቅምን በማሳደግ ረገድ የተከናወነውን ስራም በመልካም ጎኑ አንስተዋል።

በአዋጁ አፈጻጸም ወቅትም ምንም አይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለመከሰቱን ተናግረዋል።

በድንበሮች አካባቢ በቂ የቁጥጥር ስርዓት አለመኖሩንና በማህበረሰቡ ዘንድ መዘናጋቶች መኖራቸውን ደግሞ በድክመት ለይተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አዋጁ ቫይረሱ ሊያስከትል ከሚችለው ከፍተኛ ጉዳት ታድጎናል ነው ያሉት።

በማህበረሰብ አቀፍ የመከላከል፤ ምርመራና ንቅናቄ አማካኝነትም እስከታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ድረስ በመውረድ ቫይረሱን የመከላከል ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በድንበሮች አካባቢ ያለውን የሰዎች እንቅስቃሴ ለመገደብም ከክልሎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያን በቫይረሱ የከፋ ጉዳት ሳይደርስባት ወደ መጪው ዘመን ለማሸጋጋርም ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም