ድርጅቱ በ2012 በጀት ዓመት ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ አገኘ

73

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ የባህርና የሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡

ድርጅቱ በተያዘው በጀት ዓመት የተጀመሩትን ፕሮጀክቶች በማጠናቀቅ የአዳዲስ ፕሮጀክቶች ግንባታ ለመጀመርም አቅዷል። 

የኢትዮጵያ የባህርና የሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በ2011 በጀት ዓመት አጠቃላይ ገቢው 18 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የነበር ሲሆን ባለፈው በጀት አመት የ37 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ለኢዜአ እንደተናገሩት ለገቢው ስኬት በተለይ የስንዴና ማዳበሪያ ማጓጓዝ የጎላ ድርሻ ነበረው።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ድርጀቱ አጠቃላይ 11 ሚሊዮን ቶን ገቢና ወጭ የጭነት አገልግሎት መስጠቱንም ተናግረዋል።

በተያዘው የ2013 በጀት ዓመት ድርጅቱ 12 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን በማጓጓዝ 37 ቢሊየን ብር ለማግኘት አቅዶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ድርጅቱ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ከማጠናቀቅ በተጨማሪ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የድርጅቱን አሰራር ሙሉ ለሙሉ ዲጅታላይዝ ለማድርግ የተጀመሩ ስራዎችም ዘንድሮ ይጠናቀቃሉ ብለዋል።

በሞጆ ደረቅ ወደብ እየተገነቡ ያሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ከፊሎቹ በዚህ ዓመት ሲጠናቀቁ አዲስ የሚጀመሩም አሉ ነው ያሉት።

በተጨማሪ አራት ትላልቅ የስንዴና ማዳበሪያ፣ የጉምሩክ የፍተሻ ማጋዘኖች፣ በባቡሩና በወደቡ መካከል የኮንቴነር ማስተናገጃ ግንባታ እንደሚካሄድም ገልጸዋል።

የሞጆ ደረቅ ወደብ ግንባታ በአራት ምዕራፎች እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን ወደቡ በ64 ሄክታር ላይ ያለና በአንድ ጊዜ 17 ሺህ ኮንቴነር የማስተናገድ አቅም አለው ብለዋል።

ግንባታው በፋይናንስና በወሰን ማስከበር ችግር ለረጅም ጊዜ የተጓተተ ቢሆንም አሁን ላይ አፈፃፀሙ 10 በመቶ የደረሰው የድሬዳዋ ደረቅ ወደብ ግንባታም እንዲፋጠን እንደሚደረግም ነው የገጹት።

የደረቅ ወደብ መቆጣጠሪያ የአይ ሲቲ መሰረተ ልማት ግንባታም በዚህ ዓመት የሚጀመር መሆኑን አቶ ሮባ ጠቅሰዋል።

ድርጅቱ በ2011 በጀት ዓመት በባህር ትራንስፖርት 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን እንዲሁም በ2012 በጀት ዓመት 7 ሚሊዮን ቶን አጓጉዟል።


በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተለይ የአፈር ማዳበሪያና የስንዴ ምርትን ወደ አገር ውሰጥ በማጓጓዝ ቀደም ሲል ይወጣ የነበረን የውጭ ምንዛሬም አስቀርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም