ህወሃት የማተራመስ ሴራውን እንዲያቆም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብልጽግና ፓርቲ አሳሰበ

94

አሶሳ፤ ነሐሴ 7/2012(ኢዜአ) ህወሃት ህዝብን በማጋጨት የቤኒሻንጉል ጉመዝ ክልልን የማተራመስ ሴራውን እንዲያቆም የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ አሳሰበ፡፡

የፓርቲው አመራሮች በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ በአሶሳ ከተማ ለሁለት ቀናት ያካሄዱት ውይይት ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብልጽግና ፓርቲ  ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይስሃቅ አብዱልቃድር በውይይቱ ማጠቃለያ በሰጡት መግለጫ፤  ለረጅም ዓመታት ስልጣን ላይ የቆዩ አካላት ከስልጣን ሲለቁ ሃገር ለማተራመስ እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እነዚህ  አካላት ሀገር ሲመሩ በነበረበት ወቅት የህዳሴው ግድብ ግንባታ እንዲስተጓጎል አድርገው እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊው፤ የለውጥ  ኃይሉ ግድቡ ለውጤት እንዲበቃ ማድረጉንም አስታውቀዋል፡፡

ክልሉ በነጻነት ራሱን በራሱ ማስተዳደሩም ለህወሃት እንዳልተመቸው ገልጸው፤ አሁንም ህዝብን በማጋጨት  ክልሉን ለማተራመስ እየጣረ መሆኑንና ይህንን የሴራ ድርጊቱን እንዲያቆም  አሳስበዋል። 

እስከታችኛው መዋቅር ያለው የክልሉ ከፍተኛ አመራር ይህንን እውነታ በሚገባ በመረዳት ሴራውን ለማክሸፍ  በውይይቱ ትኩረት ሰጥቶ የመከረበትመሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት  የተራዘመውን ምርጫ ህወሃት አካሂዳለው ማለቱ ህገ-ወጥ መሆኑን የገለጹት አቶ ይስሃቅ ጉዳዩ በህግ አግባብ  መታየት እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡

"በክልሉ የሚገኙ አንዳንድ ተፎካካሪ ፓርዎች የሚያደርጉት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ጤናማ አይደለም" ያሉት አቶ ይስሃቅ እስከ መቀሌ በመሄድ ህዝቡን የማተራመስ ተልእኮ ከህወሃት በመውሰድ ግጭት ለመፍጠር እየሠሩ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

ህወሃት በሚመራው ክልል ምርጫ አካሂዳለው በማለት በምርጫ ሽፋን ሌላውን ክልል የማተራመስ መብት እንደሌለው መረዳት እንደሚገባም በውይይቱ አጽንኦት የተሰጠው ጉዳይ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በሃገራዊ ለውጡ ላይ ብዥታ እንደሌለባቸው ያመለከቱት አቶ ይስሃቅ "እስከመቼ ነው አጋር ሆኜ የምቀጥለው"  በሚል ለውጡን በመናፈቅ ሲታገል እንደነበረም አስታውሰዋል፡፡

የክልሉ አመራሮች ለውጡን እንዳልተቀበሉ ተደርጎ የሚናፈሰው ወሬ ስህተት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ሆኖም  ስልጣንን ለግል ፍላጎት ለማዋል በአድርባይነት የሚሠሩ ጥቂት አመራሮች የሉም ማለት እንደማይቻል ጠቅሰው በየደረጃው የሚገኘው አመራር በውጤት ብቻ የሚለካበት አሰራር ለመተግበር ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ቁርጠኛ አቋም የያዙበት ሌላው ጉዳይ ይኸው እንደሆነ አቶ ይስሃቅ አስታውቀዋል፡፡

ውይይቱ በሚቀጥሉት ቀናት በዞን፣ በወረዳ እና ከተማ አስተደዳሮች ደረጃም እንደሚቀጥል ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም