የአለም ሜትሪዮሎጂ ድርጅት በኢትዮጵያ ጽህፈት ቤት ሊከፍት ነው

3221

አዲስ አበባ ሃምሌ 4/2010 የዓለም ሜትሪዮሎጂ ድርጅት ጽህፈት ቤቱን በአዲስ አበባ ሊከፍት ነው።

ድርጅቱ አፍሪካን ለመድረስ የሚያስቸለውን ጽህፈት ቤት ለመክፈት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ዛሬ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።

የዓለም የሜትሪዮሎጂ ድርጅት በየአህጉሩ ጽህፈት ቤት አለው።

ቀደም ብሎ በሩዋንዳ የአፍሪካ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ቢቋቋምም በአገሪቷ ተከስቶ በነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ወደ ጄኔቭ ከተመለስ ዓመታት ተቆጥረዋል።

የአፍሪካ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዳግም እንዲከፈት ሲወዳደሩ ከነበሩ ሰባት የአፍሪካ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ተመርጣ ስምምነት መፈረም ችላለች።

ስምምነቱን በኢትዮጵያ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፣ በአለም የሜትሪዮሎጂ ድርጅት በኩል ደግሞ የደርጅቱ ዋና ጸሃፊ ሚስተር ፒተሪ ታላስ ፈርመዋል።

በወቅቱ የነበሩት የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሜትሪዮሎጂ ድርጅት አቶ ፈጠነ ተሾመ እንዳሉትም ከአህጉሪቱ ውጭ ሂዶ የነበረው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ወደ አህጉሪቱ መመለሱ የሚኖረው ጠቀሜታ ብዙ ነው።

ከዚህም መካከል የአገሮችን የሜትሪዮሎጂ አገልግሎት አቅም መገንባት የአህጉሪቷ አየር ሁኔታ ላይ ወቅታዊ መረጃዎችን በቶሎ ማድረስና የአገልግሎት ተደራሽነት እንደ ዋና ዋና ጠቃሜታዎች ጠቅሰዋል።

ጽህፈት ቤቱ አዲስ አበባ ላይ መሆኑ ደግሞ ኢትዮጵያ የነዚህ ቱሩፋቶች የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋትም ነው አቶ ፈጠነ የገለጹት።

ድርጅታቸው ከአልም አቀፍ ባለሙያዎችም በቅርበት ልምድ እየቀሰመ ደረጃውን የጠበቀና የአገሪቷን ኢኮኖሚ በአግባቡ መደገፍ የሚችል አገልግሎት ለመስጠት እነደሚያግዘ ተናግረዋል።