ለጋሾች ኮቪድ- 19ን ለመከላከል በሚደረገው አገራዊ ጥረት የሚያደርጉት ድጋፍ አበረታች መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ገለጹ

69

አዲስ አበባ ነሐሴ 6/2012 (ኢዜአ) በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ለጋሾች ኮቪድ-19 ን ለመከላከል ለሚደረገው አገራዊ ጥረት እያደረጉት ያለው ድጋፍ አበረታች መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናገሩ።

ስድስት የአገር ውስጥና የውጭ ተቋማት የንጽሕና መጠበቂያና የሕክምና መሳሪያዎች ድጋፍ አድርገዋል።

በዚህም ኢንጀንደርሄልዝ ኢትዮጵያ 15 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

በተጨማሪም ላየንስ ክለብ ኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን 500 ሺህ ብር የሚያወጣ የኢንፌክሽን መከላከያ፣ በፍራንክፈርት የሚገኙ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄኔራል አባላትና ሠራተኞች ከ82 ሺህ ዩሮ በላይ የሚያወጡ የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ድጋፍ ለግሰዋል።

በቻይና የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችና የኢትዮጵያ ኮሙኒቲ አባላት 20 ሺህ ዶላር የሚያወጣ የሕክምና መሣሪያዎች ለግሰዋል።

ዳይሬክት ኤይድ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ብር የሚያወጣ የሕክምና ቁሳቁስና አልባሳት እንዲሁም ጉያ ቴክስታይል 40 ሺህ ብር የሚያወጡ የሕክምና ጭምብሎችን በድጋፍ አበርክተዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት አገሪቱ ኮቪድን ለመከላከል እያደረገች ላለው ጥረት በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ለጋሾች የሚያድረጉት እገዛ አበረታች ነው።

መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር በተለይ ተቋማት፣ ግለሰቦችና ድርጅቶች እያደረጉት ያሉት ድጋፍ ወረርሽኙን ለመቋቋም እየተደረገ ያለውን  እንቅስቃሴ እየደገፈ ነው ብለዋል።

ወረርሽኙን ለመከላከል የተደረገው ድጋፍ ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን በመግለጽ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።

ማኅበረሰቡ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት እንዲያጠናከር ሚኒስትሯ ጠይቀዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ኢንጀንደር ሄልዝ ኢትዮጵያ የሰጠው 15 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የንጽሕና መጠበቂያ በተረከቡበት ወቅት እንዳሉት "ተቋሙ መንግሥት በእናቶችና ሕፃናት ላይ የሚሰራውን ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ ሲደግፍ ቆይቷል።"

ድጋፉ ለጤና ባለሙያዎችና ሕክምና በመከታተል ላይ ለሚገኙ ሴቶች እንደሚውል አስታውቀዋል።

ድጋፉ ወረርሽኙን በመከላከል ሂደት የሚስተዋሉትን የግብአቶች እጥረት ለማቃለል ያስችለዋል ብለዋል።

ሌሎችም ድርጅቶች  በተመሣሣይ  መልኩ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም