በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ኢንተርኔት ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ ይሆናል-ሚኒስቴሩ

119

አዲስ አበባ ነሀሴ 6/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ኢንተርኔት ሙሉ ለመሉ ተደራሽ እንደሚሆን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

የምርምርና ቴክኖሎጂ ውጤቶች የአገራዊ ምጣኔ ሃብት እድገቱን እንዲያፋጥኑ ይደረጋል ተብሏል።

ሚኒስቴሩ በስሩ ከሚገኙ ተቋማት ጋር የ10 አመታት መሪ እቅድና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ውይይት እያደረገ ነው።

የኢኖቬሽን ልማትና ምርምር ሚኒስትር ዘርፍ ዴኤታ አቶ ሲሳይ ቶላ እቅዱን ሲያቀርቡ እንዳሉት ኢትዮጵያ የጀመረችውን የምጣኔ ሃብት እድገት በዘመናዊ አሰራር መደገፍ የእቅዱ ትኩረት ነው።

አገራዊ ዲጂታል ምጣኔ ሃብት መገንባትና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ  የተያዘውን ዓላማ በማሳካት የዲጂታል ምጣኔ ሃብት ዝግጁነት እንደሚጎለብት አስታውቀዋል።

በዚህም የቴሌኮም ጥራት፣ ዋጋና ተደራሽነትን ማረጋገጥ የእቅዱ አንደኛው ግብ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ተደራሽነትን ከ18 ነጥብ 8 በመቶ በመጪዎቹ ዓመታት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ ይሆናል ብለዋል።

የሞባይል ተጠቃሚዎች ጥራት ያለው አገልግሎት ተደራሽነት 37 ነጥብ 2 በመቶ በእቅድ ዘመኑ መጨረሻ ሙሉ ለሙሉ እውን ለማድረግ ይሰራል።

የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ብዛትም አሁን ካለው አንድ ተቋም ወደ ሶሰት ለማድረስ መታቀዱን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ አገልግሎት መዘርጋት፣ማጎልበትና ተደራሽ በማድረግ በኩል አሁን ካለው አንድ ብሄራዊ የዳታ ክምችት ብዛት ወደ 15 ለማድረስ ታቅዷል።

በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክ ታግዘው ለህብረተሰቡ የደረሰው አገልግሎት ብዛት ከ176  በቀጣዮቹ 10 ዓመታት 2ሺህ 500 ይደርሳል።

በኦንላይን የሚሰጡ የመንግስት አገልግሎት ድርሻ በዕቅድ ዘመኑ 85 በመቶ ለማድረስ ይሰራል ብለዋል።አሁን ሁለት በመቶ አይበልጥም።

የኤሌክትሮኒክስ ግብይትን ማስፋት ሌላኛው ግብ ሲሆን 10 አዳዲስ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከላት ይኖራሉ ተብሏል።

በኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክስ ግብይትን ማስተዋወቅ 3ሺህ 500 የንግድ ተቋማትን ወደ ኤሌክትሮኒክ ግብይት ይገባሉ።

የእውቀትና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተደራሽ ከማድረግ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሺህ በላይ የለሙ የዲጂታል ዕውቀት ይዘቶች የሚገኙ ሲሆን፤ይህም በ10 ዓመታት ውስጥ ከ14 ሺህ በላይ እንደሚያድግ አቶ ሲሳይ አስረድተዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ እንዳሉት እቅዱ ኢትዮጵያ ያለችበትን ተጨባጭ የእድገት ደረጃ ታሳቢ ያደረገ ነው።

በዚህም ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ዓመታት ለመድረስ ያቀደችውን የእድገት ርእይ ከግምት ውስጥ በማስገባት በዘመናዊ አሰራር ለመደገፍ መዘጋጀቱንም አመልክተዋል።

እቅዱ ተፈፃሚነትን በሚያረጋግጥ  መነሻ መዘጋጀቱን ያስረዱት ሚኒስትሩ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመተንተን እንዲሁም ተጨባጭ መለኪያዎችንና ማሳያዎችን ጨምሮ ግቦችን ለይቶ አስቀምጧል ብለዋል።

እቅዱን ለማስፈጸም ከ4 ሺህ 200 በላይ  የሰው ሃይልና ከ157 ቢሊዮን ብር በላይ ያስፈልጋል ተብሏል።

የስራ እድልና ሃብት ፈጠራ፣ ለጠቅላላ አገራዊ ምርት የሚኖረው አበርክቶ የእቅዱ ትግበራ የሚያስገኛቸው ፋይዳዎች መለየታቸውን ዶክተር አብርሃም አስታውቀዋል።

በውይይቱ የ2013 በጀት ዓመት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ እቅድ ላይ ውይይት ተደርጓል።

ውይይቱ ነገም በመቀጠል በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ፣ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ረቂቅ ክለሳና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ውይይት ይካሄዳል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም