የፌዴራል ፖሊስ የአገሪቱን ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን እስከ ህይወት መስዋዕትነት የተከፈለበት ተግባር ማከናወኑን ገለጸ

103

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 6/2012 (ኢዜአ) የፌዴራል ፖሊስ የሀገሪቱን ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን እስከ ህይወት መስዋዕትነት የተከፈለበት ተግባር ማከናወኑን ገለጸ።

የኮሚሽኑ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ከፍተኛ አመራሮች የ2012 ዓም የሥራ አፈጻጸም ግምገማ አካሂደዋል።

የኮሚሽኑ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ከተሰጠው ተልዕኮ አንጻር ስራዎችን ገምግሟል።

በዚህም ሠላምና ፀጥታን ከማስጠበቅ፣የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከማስፈጸም ፣የልማት ድርጅቶችንና የመሰረተ ልማቶችን ከመጠበቅ ፣ የሠራዊቱን አገልግሎት አሠጣጥ ከማሳደግና የሪፎርም ሥራዎችን ወደ ተግባር ከመቀየር አኳያ የተሰሩ ስራዎች ተገምግመዋል።

አመራሮቹ የአገሪቱን ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን የተሰራው ስራ እስከ ህይወት መስዋዕትነት የተከፈለበት እንደነበርም የፌዴራል ፖሊስ የፀረ ሽብርና የተደራጁ ወንጀሎች ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር ይስሃቅ አሊ ጠቅሰዋል።

የወንጀል መከላከል ዘርፍ የምስራቅ ቀጠና ዳይሬክተር ኮማንደር ሰለሞን ከበደ በበኩላቸው ይህ ተግባር በጥንካሬ ሊጠቀስ የሚገባ መሆኑ በግምገማው ላይ መነሳቱን ገልጸዋል።

የወንጀል መከላከል ሃይል በመላው አገሪቱ እንደ መሰማራቱ የሠው ሐይል እጥረትና የሎጀስቲክ ውስንንት ስራውን በሚገባው ልክ እንዳያከናውን እጥረት በመፍጠራቸው መቀረፍ እንዳለባቸውም በግምገማው ላይ መነሳቱን ኮማንደር ሰለሞን አብራርተዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶችን ቀድሞ ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ ያሉ ውስንነቶች ከክልል የጸጥታ አካላትና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጥምረት ሊሰራበት እንደሚገባም ረዳት ኮሚሽነር ይስሃቅ አሊ ገልጸዋል።

በኮሚሽኑ የወንጀል መከላከል ዘርፍ የፀጥታና ህግ ማስከበር ዳይሬክተር ኮማንደር አህመድ አብደላም ይህንኑ ሀሳብ ነው የሚያጠናክሩት።

የጸጥታ ሀይሉ ውስን በመሆኑ እያንዳንዱ ዜጋ  የአገሪቱን ሰላም በማስጠበቁ በኩል መረጃ በመስጠትና ወንጀልን በመከላከል ስራዎች ላይ ከጸጥታ ሀይሉ  ጎን  ሊቆም ይገባል  ብለዋል። 
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ በቀጣይ ሊሰሩ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ በማስቀመጥ ግምገማውን ማጠናቀቁን ረዳት ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም