በቤሩቱ ፍንዳታ 50 ጥንታዊ ህንፃዎችን ጨምሮ 8 ሺህ ህንፃዎች ወድመዋል

66

ነሐሴ 6/2012(ኢዜአ) በሊባኖሷ ቤሩት ከተማ ወደብ ላይ በደረሰው ከባድ ፍንዳታ 8 ሺህ ሕንፃዎች መውደማቸውን የሊባኖስ ከፍተኛ እፎይታ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

እንደ ኮሚሽኑ መረጃ ከመደሙት ህንፃዎች መካከል 50 ዎቹ ጥንታዊ ናቸው፡፡

ባለፈው ሳምንት በከባዱ ፍንዳታ የደረሰውን ጉዳት በሙሉ ለማስላት እየተሰራ መሆኑንም የኮሚሽኑ ዋና ፀሐፊ መሐመድ ካይር ገልፀዋል፡፡

በከተማዋ የደረሰው ጉዳት መጠን አንዱ አካባቢ ከሌላው እንደሚለያይም ጠቁመዋል፡፡

የሊባኖስ ከፍተኛ እፎይታ ኮሚሽን ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር ለተጎዱ ወገኖች እርዳታ ማከፋል እና የአደጋ መከላከል ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡

ወደብ አቅራቢያ በሚገኘው መጋዘን ውስጥ በቸልተኝነት የተከማቸው 2 ሺህ 750 ቶን አሞኒየም ናይትሬት ለ175 በላይ ዜጎች ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡

የቤሩት ፍንዳታ የኢኮኖሚ ቀውስ እና የኮኖና ቫይረስ ወረርሺኝ ሊባኖስ ጫና ውስጥ በገባችበት ወቅት ነው የደረሰው፡፡

ተቃዋሚዎች ባለፉት ሁለት ቀናት የፀረ-መንግስት ሰልፎችን በማካሄድ ከፖሊስ ጋር ግጭት ፈጥረዋል፡፡

በሊባኖስ የተባበሩት መንግስታት ልዩ አስተባባሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀሰን ዲያብ እና ካቢኔያቸው ስልጣን ከለቀቁ በኋላ የሊባኖስ ባለሥልጣናት በፍጥነት አዲስ መንግስት እንዲመሰርቱ ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡

ልዩ አስተባባሪው ጃን ኪቢስ በሰጡት መግለጫ የሊባኖስ ህዝብ ምኞትን የሚያሟላ እና ሀገሪቱ ያጋጠሟትን አጣዳፊና ፈታኝ ችግሮች ሊፈታ የሚችል አዲስ መንግስት እንዲመሰረት ጠይቀዋል፡፡

ሀገሪቱ ከገጠማት ችግር እንድትወጣ በሚል ጠቅላይ ሚኒስትር ሀሰን ዲያብ እና ካቢኔያቸው ስልጣን ከለቀቁ በኋላም የተቃውሞ ሰልፎች መቀጠላቸውን የአናዶሉ ዘገባ ይጠቁማል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም