ኢትዮጵያ ውስጥ በሚተገበሩ ፖሊሲዎች ላይ የሚደረገው የትግበራና ውጤታማነት ጥናት ደካማ ነው ተባለ

73
አዲስ አበባ ሃምሌ 4/2010 በኢትዮጵያ ሥራ ላይ የሚውሉ ፖሊሲዎችን የትግበራ ሂደትና ውጤታማነት ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ደካማ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ገለፁ። የፖሊሲ ግምገማ ማካሄድ ውጤታማነትን ከማረጋገጥ ባሻገር የኃብት ብክነትን ለማስወገድ፣ ምጣኔ ኃብታዊ ዕድገትን ለማፋጠንና ከህዝብ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ለመቀነስ ያግዛል ሲሉም ምሁራኑ ተናግረዋል። ፖሊሲዎች ግባቸውን ማሳካት የሚችሉት የትግበራ ሂደታቸውን በአግባቡ በመገምገም የማስተካከያ እርምት ሲወሰድ እንደሆነም ገልጸዋል። ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖሊሲ ጥናትና ምርምር እንደዚሁም የምጣኔ ኃብት ምሁራን እንደገለፁት ግን በኢትዮጵያ ለፖሊሲዎች ውጤታማነት መሰረት ለሆነው ለዚህ ጉዳይ የተሰጠው ትኩረት አናሳ ነው። በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲ ጥናት ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ተባባሪ ፕሮፌሰር ደረጀ ተረፈ እንዳሉት ሥራ ላይ የሚውሉ ፖሊሲዎች የትግበራ ሂደት የሚገመገመው የማሻሻያ እርምጃዎችን በመውሰድ ውጤታማነታቸውን ለማረጋገጥ ነው። በጥናትና ምርምር ተደግፎ በሚካሄደው ግምገማ መሰረት ፖሊሲዎቹ የታለመላቸውን ግብ ማሳካት ካልቻሉ ደግሞ በአዲስ መተካትም ሌላው የፖሊሲ ግምገማ ዓላማ መሆኑን ተናግረዋል። የፖሊሲ ጥናት ግምገማ ውጤቶችንም ለህዝቡና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ማሳወቅም  እንደሚያስፈልግ አክለዋል። ከእነዚህ አሰራሮች አኳያ ታዲያ በአገሪቱ ፖሊሲዎችን በአግባቡ የመገምገምና ውሳኔ የመስጠት ልምድ አነስተኛ መሆኑን ነው ተባባሪ ፕሮፌሰር ደረጃ ያብራሩት። በኢትዮጵያ ሥራ ላይ የዋሉ ፖሊሲዎች የትግበራ ሂደትን በጥናትና ምርምር የመገምገም ልምዱ አነስተኛ በመሆኑ ጠንካራና ደካማ ጎናቸው ያልተለዩ ፖሊሲዎች ሥራ ላይ መኖራቸውንም ተናግረዋል። እንደዚህ ዓይነቱ አሰራርም የኃብት ብክነት፣ የሕብረተሰብ ፍላጎቶች ያለመሟላትና ሰላምና መረጋጋት እጦት የሚፈጥር በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። የፖሊሲ ግምገማ ማካሄድ ውጤታማነትን ከማረጋገጥ ባሻገር የኃብት ብክንነትን ለማስወገድ፣ ምጣኔ ኃብታዊ ዕድገትን ለማፋጠንና ከህዝብ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ለመቀነስ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል። የፖሊሲ ግምገማዎች ለማካሄድ በዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል፣ ጊዜና በጀት አስፈላጊ መሆኑንም አክለዋል። ከፖሊሲ ትግበራ ጋር በተያያዘ በተለያዩ ወቅቶች የሚወሰዱ እርምጃዎችና አቅጣጫዎች በተሟላ ግምገማ ተመስርተው መሆናቸው አጠያያቂ ነው ሲሉም ተናግረዋል። በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ኃብት ትምህርት መምህር አቶ ብርሃኑ ያደቴ በበኩላቸው የህዝብ ፍላጎት በየወቅቱ ከሚፈጠሩ አዳዲስ ሁነቶች ጋር የሚቀያየር በመሆኑ ፖሊሲዎች የተቀመጠላቸውን ግብ በጊዜ ገደባቸው ከማሳካት አንፃር የሚያጋጥሙ ጠንካራና ደካማ ጎንና ያስገኙት ውጤት መለየት አለበት ብለዋል። በምጣኔ ኃብት ልማት ዙሪያ ተቀርፀው ትግበራ ላይ ያሉ ፖሊሲዎች ችግር ፈቺ ሆነው የህዝቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዲችሉ የማሻሻያ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባም ነው አቶ ብርሃኑ የገለፁት። በኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል የኢንደስትሪ ጥናትና ምርምር ዘርፍ አስተባባሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለበል ደሴ  እንዳሉት በአገሪቷ  ብዙ ርቀት ሊወስዱ የሚችሉ በርካታ ውጤታማ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ቢኖሩም ከአፈፃፀም ጋር በተያያዘ ግን በርካታ ድክመቶች አሉ። በመሆኑም ማዕከሉ በፖሊሲ አፈጻጸም ላይ ያሉ ክፍተቶችን የመለየትና የመፍትሄ ሀሳቦችን የማቅረብ ስራዎችን ቅድሚያ በመስጠት በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል። ማዕከሉ አሁን ባለው አቅም የግብርና፣  የምጣኔ ኃብታዊ፣ የኢንዱስትሪና የከተማ ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ትግበራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል። የተቋማት የአቅም ግንባታ፣ የመልካም አስተዳደርና ማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፎች የትግበራ ሂደትም በማእከሉ ትኩረት የተሰጣቸው ሌሎች ጉዳዮች ናቸው ብለዋል። በዚህም መሰረት በዘርፎቹ የፖሊሲ አተገባበር ላይ ጥናት በማካሄድ የተለዩት ክፍተቶችና የተጠቆሙት የመፍትሄ አቅጣጫዎች ለአስፈጻሚ አካላት እንዲቀርቡ መደረጉንም ገልፀዋል። በቀጣይም አዲስ የፖሊሲ ሀሳቦችን የማቅረብና የማሻሻያ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል ነው ያሉት። በአገሪቱ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር  አቅም ደካማ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው ማዕከሉ የፖለሲ ሀሳቦችን የማመንጨት ኃላፊነቱን ለመወጣት በባለሙያዎች ብቃት፣  ልምድና ቁጥር አላደገም ብለዋል። ይህንን ለመለወጥ የሚያስችሉ እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚገባም ተናግረዋል። አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳሉት መንግስታዊ የሆነው ማዕከሉ ፖሊሲዎችን ወቅታዊ የማድረግ፣ በየጊዜው እያደገ ከሚመጣው የልማትና የዲሞክራሲ ፍላጎት ጋር የማጣጣም፣ ውጤታማነታቸውንም የመገምገምና እንደአስፈላጊነቱ ደግሞ በአዳዲስ የፖሊሲ አቅጣጫዎች የመተካት ሥራዎችን በሰፊው ማከናወን ይጠበቅበታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም