ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ የአረንጓዴ አሻራ በስኬት እንዲካሄድ ተሳትፎ ላደረጉት ምስጋና አቀረቡ

71

ነሐሴ 6/2012 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ በስኬት እንዲካሄድ ተሳትፎ ላደረጉ ዜጎች ምስጋና አቅርበዋል።

ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የመዝጊያ ስነ ስርዓት በባህር ዳር ከተማ እየተከናወነ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም በባህር ዳር ከተማ ቤዛዊት ቤተ-መንግስት እየተከናወነ ባለው የመዝጊያ ስነ ስርዓት ተገኝተዋል።

በስነስርዓቱ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት በሁለተኛው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሀ ግብር 5 ቢሊዮን ችግኝ በመትከል እቅዱን ቀድሞ ማሳካት ተችሏል።

መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የተሰጠውን አደራ ተቀብሎ በእኔነት ስሜት እቅዱን ቀድሞ ማጠናቀቅ በመቻሉ ምስጋና አቅርበዋል።

''ጭቃ ሳይነኩና ችግርን ሳይጋፈጡ ሀገርን ማበልፀግ አይቻልም'' ያሉት ዶክተር አብይ መላው ኢትዮጰያውያን ለችግኝ ተከላው ያሳዩትን ቁርጠኝነት በሌሎች የልማት ስራዎችም ሊደግሙት እንደሚገባም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በሚቀጥለው አመት ደግሞ ስድስት ቢሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉ ገልጸው፤ "የሚቀጥለውን አመት ለየት የሚያደርገው ለጎረቤቶቻችን አንድ ቢሊዮን ችግኞችን የምናዘጋጅ መሆኑ ነው" ብለዋል፡፡

እኛም ብቻ ሳንሆን ጎረቤቶቻችን የሚተክሉት ችግኝ ሀገር ለም ከማድረግ አልፎ የቀጠናውን ስነ ምህዳር ለመጠበቅ ከፍተኛ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአመቱ የታቀደው 5 ቢሊዮን ችግኝ የመትከል እቅድ መሳካቱን ገልጸው፤ ከአተካከል ጋር ተያይዞ ሳይፀድቁ የሚቀሩ ችግኞችን ለመተካት ተጨማሪ 200 ሚሊዮን ችግኞች በዚህ ነሃሴ ወር ይተከላሉ ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው በክልሉ ከ1.6 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል።

ይህም የእቅዱ 105 በመቶ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአራት ዓመት ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል አቅድ መያዟ ይታወሳል፡፡

በዛሬው የአረንጓዴ አሻራ የ2012 ዓ.ም ማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ በቤዛዊት ተራራ የወይራ እና ዝግባ ችግኝ ተከላ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በመርሃ ግብሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ ና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎችም ቤዛዊት ተራራ ላይ ሀገር በቀል ችግኞችን እየተከሉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም