ህዝብን የሚያወናብዱ የህወሓት አመራሮችን መታገል ይገባል

61

አዲስ አበባ ነሀሴ 5/2012  (ኢዜአ) የግል ጥቅማቸውን  ለማስጠበቅ ህዝብን የሚያወናብዱ የህወሓት አመራሮችን መታገል ይገባል ሲሉ  የትግራይ የብልጽግና ፓርቲ አባላት ተናገሩ።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ በክፍለ ከተማው ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጅ አባላቱ ጋር ዛሬ ተወያይቷል፡፡

በውይይቱም ህወሓት የትግራይን ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር ለመነጠል እየሰራ መሆኑ ተነስቷል፡፡

መንግስት ህወሓት እየሄደበት ያለውን ህጋዊ ያልሆነ አካሄድ ስርዓት ማስያዝ እንዳለበትም ተወያዮቹ በመድረኩ ጠቁመዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጊዜያዊ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሐፍታይ ገብረእግዚአብሔር የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ  ህዝብን የሚያወናብዱ የህወሓት አመራሮች ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ፤የትግራይ ህዝብም በአንድነት ቆሞ ሊታገላቸው ይገባል ብለዋል፡፡

"የብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያዊነትንና የብሔር ማንነትን አጣጥሞ የሚሄድ ተራማጅ ድርጅት ነው፤ የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር እኩል ተጠቃሚ እንዲሆንም እየሰራ ነው" ብለዋል፡፡

የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ ሙሉቀን ሀብቱ በበኩላቸው የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያ ምስረታ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸው "ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አንድ ናቸው የሚለው ፕሮፓጋንዳ ህዝቡን ከመናቅ የመነጨ ክህደት ነው" ብለዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የተሳተፉና በክፍለ ከተማው የሚኖሩ የትግራይ ተወላጅ የብልጽግና ፓርቲ አባላት በበኩላቸው፣ የትግራይ ህዝብ ባልተገባ ትስስር ዝርፊያ ሲፈጽሙ በነበሩ የህወሓት አመራሮች ምክንያት ካለ ስሙ ስም ሲሰጠው መቆየቱን አስታውሰዋል።

የህወሓት አመራሮች ወጣቱን ለስደት፤ ነዋሪውን ደግሞ ለችግር በመዳረግ ለከፋ የጭቆና ቀንበር እየደረጉት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ህወሓት የትግራይ ህዝብን ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ለመነጠል እየሰራ መሆኑን ያስታወሱት አባላቱ፣ በትግራይ ህዝብ ላይ የጫነውን የአምባገነን ስርዓት በአንድነት ለመታገል ቁርጠኛ ነን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም