ኢትዮጵያና ሳዑዲ በህገ ወጥ መንገድ የሚደረግን ጉዞ ለመከላከል የጋራ ጥረት ጀምረዋል

69

ነሓሴ 5/2012 የኢትዮጵያና ሳዑዲ አረቢያ መንግስታት በየመን በኩል ወደ ሳዑዲ የሚደረገውን የኢትዮጵያዊያን ህገ ወጥ ጉዞ ለመግታት እየሰሩ መሆኑ ተገለጸ።

በበየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በየመን አቋርጠው ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንደሚገቡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት በህይወታቸው ላይ አደጋ የጋረጠና ብዙ ውጣ ውረድ የተሞላበት እንደሆነ ይታወቃል።

በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አብዱልአዚዝ አህመድ እንደሚሉት ወደ ሳዑዲ ከሚገቡት ኢትዮጵያውያን መካከል በህገ ወጥ መልኩ በየመን በኩል የሚጓዙት ከ80 በመቶ በላይ ድርሻ ይይዛሉ።

በርካታ ኢትዮጵያውያን የተሻለ ኑሮና ህይወት ፍለጋ በማሰብ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመግባት በሚያደርጉት ጥረት በርካታ እንግልትና ስቃይ ይገጥማቸዋል።

በጉዞው ህይወታቸውን አጥተው መንገድ ላይ የሚቀሩም አሉ።

በችግሩ አሳሳቢነት ላይ የተግባቡት የኢትዮጵያና ሳዑዲ አረቢያ መንግስታት መፍትሄ ለማበጀት የተለያዩ ተግበራትን በማከናወን ላይ ይገኛሉ።

በመሆኑም በየመን አድርገው ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን የሚፈልሱባቸውን ቦታዎች የመለየት ለማቋቋም የሚችሉበት ሁኔታ ላይ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ከሳዑዲ የሚመለሱ ዜጎችም በኢትዮጵያ በዘላቂነት መቋቋም ማስቻልም በአገራቱ እንደሚከናወን ነው አምባሳደር አብዱልአዚዝ ያስረዱት።

በጉዳዩ ዙሪያ ከሳዑዲ አረቢያ መንግስት ጋር ተከታታይ ውይይቶች መካሄዳቸውንና ያለው ሂደት ጥሩ የሚባል እንደሆነ ተናግረዋል።

በሁለቱ አገሮች ችግሩን ለመፍታት የሚያስችሉ የጋራ እቅዶች እየተዘጋጁ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር አብዱልአዚዝ በቀጣይ በጉዳዩ ዙሪያ የስምምነት ፊርማ ይኖራል ብለዋል።

በሚደረሰው ስምምነት መሰረት እ.አ.አ 2020 ወደ ስራ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቀም ነው የገለጹት።

በተያዘው ዓመት በየመን አቋርጠው ወደ ሳዑዲ አረቢያ ከ16 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን እንደገቡና በርካቶቹ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት በኋላ የመጡ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ሆኖም ኤምባሲው ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመሆን ወደ አገራቸው የመመለስ ተግባር እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በሳዑዲ አረቢያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ወደ ሳዑዲ የሚጓዙ ዜጎች ፍላጎት ስራ ማግኘት የተሻለ ህይወት ማግኘት እንደሆነ ለአገሪቷ መንግስት እንዲገነዘብ የማድረግ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት ዜጎች ወደ አገራቸው ለለመለስ የሚወጣው ወጪ በራስ አቅም የሚሸፈን ነበር።

ላለፉት ሁለት ዓመታት ግን የሳዑዲ አረቢያ መንግስት በራሱ ወጪ ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ ተግባር እያከናወነ መሆኑን ነው አምባሳደር አብዱልአዚዝ ያስረዱት።

በሌላ በኩል ሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ዜጎችን በአንድ ቦታ በማጎር ህገ-ወጥ ስራ እንዲሰሩ የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን እንዳሉም ደርሰንበታል ብለዋል።

በዚህ ጉዳይ ተሳታፊ ሆነው የተገኙትን በማጣራት ኤምባሲው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።

በሳዑዲ ችግር የገጠማቸውን ዜጎች የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ አባላት ጋር በመሆን መጠለያና ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም አምባሳደሩ ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ባለፉት ሁለት ዓመት 200 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ወደ አገራቸው መመለሳቸውንም ገልጸዋል።

የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) "የሚመጣውን ጉዳት ባለማገናዘብ ለማደግ ያለ ፍላጎት" በሚል ርዕስ በየመን በኩል በህገ ወጥ መንገድ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያንን አስመልክቶ ያሳተመው የጥናት በግንቦት 2012 ዓ.ም ይፋ አድርጎ ነበር።

በጥናቱ ላይ እ.አ.አ ከ2017 ጀምሮ ከ400 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን የመንን አቋርጠው ወደ ሳዑዲ አረቢያ መግባታቸውንና እ.አ.አ በ2019 ከ120 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ አገራቸው መመለሳቸው ተገልጿል።

ድርጅቱ በየመን አድርገው ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመግባት በጅቡቲ ኦቦክ ከተማ ያገኛቸውን ከሁለት ሺህ በላይ ወጣቶች አነጋግሮ ከነዚህ ውስጥ በጀልባ ገብቶ የመስጠም አደጋን የሚረዱት ከ50 በመቶ በታች የሚሆኑ ናቸው ብሏል።

በጥናቱ ቃለመጠይቅ ከተደረገላቸው ወጣቶች መካከል ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚሄዱት በኢኮኖሚና ማህበራዊ ምክንያቶች እንደሆነ ገልጸዋል።

ቃለመጠይቅ ከተደረገላቸው 64 በመቶው ከዚህ በፊት ሳዑዲ አረቢያ ለመሄድ በትንሹ ሁለት ጊዜ ሞክረው እንደነበር ተናግረዋል።

83 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ለመሄድ የሚወስኑት ጉዞ ከመጀመራቸው ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ እንደሆነና 59 በመቶ የሚሆኑትም ከመሄዳቸው በፊት ለቤተሰቦቻቸው አለማሳወቃቸውን  በጥናቱ ላይ ተመላክቷል።

ኢትዮጵያውያን ዜጎች በተሳሳተ መረጃ ራሳቸውን ጉዳት ላይ እንዳይጥሉ ትክክለኛውን መረጃ የመስጠትና ለጉዟቸው ምክንያት የሚያደርጓቸው ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመቀነስ እንደሚያሰችል ድርጅት በምክረ ሀሳብነት አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም