በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሳውላ ካምፓስ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ነው

69
አርባምንጭ ሀምሌ 4/2010 በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሳውላ ካምፓስ በ190 ሚሊዮን ብር እየተካሄደ ያለው ግንባታ 88 በመቶ መጠናቀቁ ተገለፀ ፡፡ የካምፓሱ አስተባባሪ አቶ ገብረመድህን ጫመኖ  እንደገለጹት በ2006 ዓ.ም ማጠናቀቂያ ላይ መሠረት ድንጋይ የተጣለለት የሳውላ ካምፓስ በ2007 13 ትላልቅ ህንፃዎችን ገንብቶ ማጠናቀቅ ችሏል ፡፡ ካምፓሱ የመማሪያ ክፍሎች፣ ማደሪያና፣ የመምህራንና የአስተዳደር ቢሮዎች፣ እንዲሁም ካፍቴሪያና ቤተ መጻህፍት ግንባታን በማጠናቀቅ በ2008 ዓ.ም 194 ተማሪዎችን ተቀብሎ የመማር ማስተማር ስራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ቀሪ የመማሪያ ፣ የቤተ መጻህፍት ፣ የቤተ ሙከራና ካፍቴሪያ ህንፃዎች እንዲሁም የውስጥ ለውስጥ መንገዶችና ዙሪያ አጥር በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁ ገልጸዋል፡፡ በብራይት ዩናይትድ ኮንስትራክሽን ድርጅት እየተገነባ ያለው የሳውላ ካምፓስ በውሉ መሠረት በተያዘው ዓመት መጨረሻ እንደሚጠናቀቅ አስታውቀዋል፡፡ በዚሁም ተማሪዎች የመማሪያ፣ የቤተ መፃህፍትና ቤተ ሙከራ አገልግሎትን በስፋት እንዲያገኝ ከማስቻልም በላይ አዳዲስ የትምህርት ክፍሎችን ለመክፈት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡ በዚሁ መሠረት በ2011 በመደበኛው ፕሮግራም በ10 የትምህርት ክፍሎች ከ500 በላይ አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪ ብዙነህ ንጉሤ በሰጠው አስተያየት ካምፓሱ አዲስ በመሆኑ ከመማሪያ፣ ከቤተመፃህፍት እና ከቤተ ሙከራ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ባልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ መቆየቱን ገልጿል ፡፡ አሁን እየተገነቡ ያሉ ህንፃዎች ሲጠናቀቁ በመጪው ዓመት ለሚማሩ ተማሪዎች ምቹ እንደሚሆንም ጠቁሟል ፡፡ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ  ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ፍሰሃ በቀለ ተቋሙ በአርባ ምንጭ ከተማ አምስት ካምፓሶች እንዳሉት ጠቅሰው ሳውላ ካምፓስ ስድስተኛውና የብዙዎችን ጥያቄ የመለሰ መሆኑንም ጠቁመዋል ፡፡ በ2008 ዓ.ም 194 ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የጀመረው የሳውላ ካምፖስ በ10 የትምህርት ክፍሎች ካስተማራቸው አንድ ሺ 141 ተማሪዎች መካከል ዘንድሮ የመጀመሪያዎቹን 130 ተማሪዎች አስመርቋል ፡፡ በአገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ታሪክ ከመጀመሪያዎቹ ተርታ የሚሰለፈው አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ ለ31ኛ ጊዜ ያስመረቃቸውን ጨምሮ 48 ሺህ 365 ምሩቃንን አፍርቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም