በደቡብ ክልል የኮሮና ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ሁሉም ሊረባረብ ይገባል

50

ሀዋሳ ነሐሴ 4/2012 (ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የከፋ አደጋ ሳያስከትል ለመቆጣጠር በተጀመረው ስራ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊረባረብ እንደሚገባ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አሳሰቡ። 

"ማንም" የተሰኘ ለአንድ ወር የሚቆይ ክልላዊ  የኮሮና ቫይረስ የማህበረሰብ ንቅናቄ እና የምርመራ ዘመቻ ይፋዊ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር  ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተካሄዷል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ስነ-ስርዓት  ወቅት  የቫይረሱ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል፤ ስርጭቱን ለመግታት በተጀመረው ሥራ  ለጤና ባለሙያዎች ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁሉም በጋራ ሊረባረብ ይገባል ብለዋል፡፡

ክልሉ ከተለያዩ ክልሎች፣ በውጭ ደግሞ ከኬንያና ደቡብ ሱዳን ስለሚዋሰን ፣ እንዲሁም በንግድና በሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ከአዲስ አበባ ካለው ቁርኝት የተነሳ ተጋላጭነቱ ከፍተኛ እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡

እስካሁን  የቫይረሱ ስርጭት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ በቂ መረጃ እንደሌለ ያመለከቱት አቶ ርስቱ ይህ ዘመቻ የስርጭት መጠኑንና በቀጣይ ሊወሰዱ ስለሚገቡ ርምጃዎች አመላካች ውጤቶች የሚጠበቅበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዘመቻው የስርጭት መጠኑን ለማወቅና  የምርመራ አቅም ለማሳደግ በአትኩሮት የሚሠራ መሆኑን አስረድተዋል።

በየደረጃው  ያለው መዋቅር በመናበብ አስፈላጊ ግብአቶችን በማሟላትና የጤና ተቋማትን በማደራጀት የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣት አለበትም ብለዋል፡፡

በህዝብ ትራንስፖርት፣ ኃይማኖት ተቋማትና የግብይት ስፍራ የሚስተዋለውን ክፍተት ለማረም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም አንጻር  ማስተካካል እንደሚገባም  አቶ ርስቱ አመልክተዋል፡፡

እስካሁን በሃገር ደረጃ በቫይረሱ ከተያዙት ውስጥ 92 በመቶ ምልክት ያላሳዩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ምክትል ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ ናቸው።

 ይህ ደግሞ የቫይረሱን ስርጭት ለመገመት አስቸገሪ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

"በቂ መረጃ እንዲኖረን ማህበረሰባችንን በማነቃነቅ ግንዛቤ ለመፍጠርና የመመርመር አቅምን ለማሳደግ ዘመቻው ከፍተኛ ዕድል ስለሚኖረው የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አቅናው ካውዛ በበኩላቸው በክልሉ ለምርመራ ያለው ቁርጠኝነት ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸው ዘመቻውን ውጤታማ ለማድረግ መተባበርና ያስፈልጋል ብለዋል።

የምርመራ ላቦራቶሪዎች ቁጥር ከነበረው ከፍ ለማድረግ በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅቱ መጠናቀቁን አመልክተዋል፡፡

በክልል ደረጃ በሚካሄደው በዚህ ዘመቻ ከ28 ሺህ ነዋሪዎች በላይ ምርመራ ለማድረግ መታቀዱን አስታውቀዋል።

ክልላዊ ማህበረሰብ አቀፍ የንቅናቄና የምርመራ ዘመቻ ከ11 ሚሊዮን በላይ የክልሉ ነዋሪ ስለቫይረሱ መረጃ ተደራሽ ለማድረግም ታቅዷል።

በዘመቻው ማስጀመሪያ መርሃ ግብር  የክልሉ፣ የዞኖችና የከተማ አስተዳደሮች የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም