የሕወሐት ምርጫ ችግር ከማስከተሉ በፊት መንግሥት ማስቆም አለበት-ምሁራን

79

አዲስ አበባ ነሐሴ 4/2012 (ኢዜአ) -በትግራይ ክልል ሕወሐት አካሂደዋለሁ የሚለው ምርጫ ችግር ከማስከተሉ በፊት የፌዴራሉ መንግሥት ሕግን በማስከበር ድርጊቱን ሊያስቆም እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሕግ ምሁራን ገለጹ።

በኢትዮጵያ በያዝነው ወር ሊካሄድ ታስቦ የነበረው ብሔራዊ ምርጫ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በሕገ-መንግሥት ትርጉም እንዲራዘም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰኔ 3/2012 ዓ.ም መወሰኑ ይታወቃል።

ሆኖም የትግራይ ክልል መንግሥት በሕገ-መንግሥት ትርጉም ከተወሰነው በተቃራኒ ምርጫ ለማካሄድ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ክልል መንግሥት ምርጫ ለማካሄድ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ "በአፋጣኝ እንዲያቆም" በደብዳቤ  ማሳሰቡም ይታወቃል።

ክልሉ ሕገ-መንግሥታዊ  ሥርዓቱን አደጋ ላይ በሚጥል ድርጊቱ የሚቀጥል ከሆነ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ- መንግሥቱ እና በሌሎች ሕጎች የተሰጠውን ሥልጣን ለመተግበር እንደሚገደድም አስጠንቅቋል።

የትግራይ ክልል ምክር ቤት በጻፈው ምላሽ ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በትግራይ ክልል ስለሚካሄደው ምርጫ የጻፈው ደብዳቤ “ሕጋዊ ውጤት ሊያስከትል አይችልም” ብሏል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲ የሕግ ምሁራን እንደሚሉት በምርጫ ጉዳይ በሕገ-መንግሥቱ ሥልጣን የተሰጠው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመሆኑ ሕወሐት ይህንን ሕግ ሊቃረን አይገባውም።

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሕግና ፌደራሊዝም መምህሩ ዶክተር ምሥጋናው ክፈለው እንዳሉት የትግራይ ክልል በምርጫ ጉዳይ ቅሬታ ካለው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርቦ ነው ውሳኔ የሚሰጠው።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከዚህ ቀደም ያሳለፋቸው ውሳኔዎች እና አሁን ለክልል የላከው ማስጠንቀቂያም ሕገ-መንግሥታዊ መሠረት ያለው ነው ብለዋል።

በኮተቤ ሜትርፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የሕግና የታሪክ መምህር ዶክተር አልማው ክፍሌ በበኩላቸው ከትግራይ ክልል ምርጫ ጀርባ ፖለቲካዊ አጀንዳዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

የትግራይን ሕዝብ “ልትወረር ነው” በሚል ፖለቲካዊ ቁማር ሥልጣኑን ለማራዘም፣ ሕዝብን ከመንግሥት ጋር ለማጣላት፣ በሕገ-ወጥ መንገድ የወሰዳቸውን መሬቶች ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት አልሟል ነው ያሉት።

ሕወሐት ምርጫ እያለ ችግር ከመፈጠሩ በፊት የፌዴራሉ መንግሥት ሕግ የማስከበር ተግባሩን የማከናወን ግዴታ አለበት ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ የፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ ገብቶ የክልሉን ሕዝብ ከግፍና ችግር ማዳን አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም