የጦር መሳሪያ ምዝገባ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

89

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 4/2012(ኢዜአ) ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል ሲባል የጦር መሳሪያ ምዝገባ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ተናገሩ።

ምዝገባው ከመጀመሩ በፊት ግን ህብረተሰቡን የማወያየት ሥራ ይከናወናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያን ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር በወጣው አዋጅ ላይ የጦር መሳሪያ ያላቸው ዜጎች የጦር መሳሪያቸውን ህጋዊ ለማድርግ በሁለት ዓመት ውስጥ ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል።

በመሆኑም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አዋጁን ተፈፃሚ ለማድረግ የፀጥታ አካላትን በማስተባበርና ሌሎችንም ተግባራት በማከናወን ላይ መሆኑን ወይዘሮ ሙፈሪያት ተናግረዋል።

ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ዓለም አቀፍ ሰንሰለቱ የበዛ ወንጀል በመሆኑ በሁሉም የሀገሪቱ ድንበሮች የቁጥጥር ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

በሀገሪቱ እስካሁን መሳሪያን የመሸጥና የማከፋፈል ህጋዊ ፈቃድ በሌለበት ሁኔታ መሳሪያን የመያዝ ልምድ በሰፊው እየተስተዋለ ይገኛልም ነው ያሉት።

የጦር መሳሪያ መያዝ እንደ ባህል የሚታይባቸው አካባቢዎች መኖራቸው ደግሞ ቁጥጥሩን አዳጋች እንዳደረገው አስረድተዋል።

መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት የጦር መሳሪያ ምዝገባ ለማካሄድ የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ለምዝገባው የሚረዱ የመረጃ ቴክኖሎጂ ሶፍትዌር ማበልፀግ፣ አሰራርና አደረጃጀት የመፍጠርና ሌሎችም ምቹ ሁኔታዎች ተጠናቀዋል ብለዋል።

ሆኖም ምዝገባውን ከማካሄድ አስቀድሞ ከህዝብ ጋር የሚከናወኑ የውይይት መድረኮች መኖራቸውን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

በመሳሪያ ዝውውርና ባለቤትነት ላይ ህጋዊ የሆነ መሰረት እንዲኖርና ህገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል ሥርዓት ለመዘርጋት ዓለም አቀፍ ተቋማትን ያሳተፈ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ፤ አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተው አሁን የቀረው በአዋጁ ጠቀሜታ ላይ ከህብረተሰቡ ጋር ተከታታይ ውይይት ማድረግ ነው።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ጌቱ ተክለዮሃንስ እንዳሉት፤ የፀጥታ አካላት ህገ ወጥ የሆኑ ጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል ጥብቅ የሆነ ቁጥጥር እያደረጉ ነው።

ይሁን እንጂ  ወንጀሉ ውስብስብ በመሆኑ አሁንም ከገጠር እስከ ከተማ የዝውውር ሰንሰለት መኖሩን ጠቅሰዋል።

ህገ ወጥ የጦር ማሳሪያ አገርን የሚጎዳና ህዝቡን ስጋት ላይ የሚጥል በመሆኑ ህግ እንዲተገበር ህዝቡ ከፅጥታ አካሉ ጋር በትብብር እንዲሠራ ጠይቀዋል።

የፀጥታ አካላት ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ከምንጩ ለመከላከል እስካሁን እያደረጉት ያለው ሥራ ውጤታማ መሆኑንና ብዙ ህገ ወጥ መሳሪያዎችም መያዛቸውንም ገልጸዋል።

የፌደራል ፖሊስ አዋጁን ከሚያስፈፅሙ አካላት አንዱ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ በአዋጁ መሰረት ወንጀልን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም