በቢሊዮን የሚቆጠር የዓለም ህዝብ በውሃ ችግር ኮሮናን መከላከል እያቃተው ነው

105

አዲስ አበባ ነሀሴ 4/2012 (ኢዜአ) በዓለም ላይ ከ3 ቢሊዮን በላይ ሰዎች የውሃ ችግር ስለገጠማቸው ኮቪድ-19ን ለመከላከል አዳጋች ሆኖባቸዋል፤ የቫይረሱ ስርጭት በየእለቱ እየተስፋፋ መምጣቱንም መረጃዎች ያመለክታሉ።

በዓለም ላይ ከአምስት ሰዎች ሁለቱ ለመጠጥ ወይም ለመታጠቢያ የሚሆን ውሃ ለማግኘት በእጅጉ ይቸገራሉ ይላል የብሉምበርግ ዘገባ።

በመሆኑም አሁን ላይ 3 ቢሊዮን የአለም ህዝብ ንጽህናውን ለመጠበቅ የሚያስችለው ውሃ እንዲሁም ሳሙና ማግኘት አይችልም።

ይህ መሆኑ ደግሞ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ እየተስፋፋ የመጣውን ኮቪድ-19 ለመከላከል እንዳይችሉ አንደኛው ተግዳሮት ሆኗል።

በተለይ የከተማ ነዋሪዎች ውሃ ለማግኘት ሲሉ በተወሰኑ አካባቢዎች በርከት ብለው ስለሚገኙ ለቫይረሱ መዛመት ምክንያት መሆኑ አይቀርም።

መንግስታት ለውሃ መሰረተ ልማት የሚመድቡት ገንዘብ ዝቅተኛ በመሆኑ ችግሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚፈታ አለመሆኑን መረጃው አመልክቷል።

እንደ ብሉምበርግ ዘገባ ከሆነ በረካታ የዓለማችን ህዝቦች የውሃና የንጽህና መጠበቂያ ሳሙና እጥረት እየገጠማቸው በመሆኑ ቫይረሱን መከላከል እየቻሉ አይደለም።

ለችግሩ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ትብብር የሚያስፈልግ ሲሆን ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀትም ዘላቂ ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል ብሏል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በየአመቱ 4 ቢሊዮን የአለም ህዝብ ቢያንስ ለአንድ ወር ያክል የከፋ የውሃ ችግር ያጋጥመዋል።

ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ካልተሰጠው እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ2050 ከ5 ነጥብ 7 ቢሊዮን በላይ የዓለም ህዝብ ተመሳሳይ የውሃ ችግር ያጋጥመዋል ተብሎ ይገመታል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እኤአ በ2030 ዘላቂ የውሃ መሰረተ ልማትን ለማሟላት 6 ነጥብ 7 ትሪሊዮን ዶላር  ያስፈልጋል ብሏል ።