15ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በሚከበርበት ዙሪያ ውይይት ተጀመረ

52

ድሬዳዋ ነሐሴ 4/2012(ኢዜአ) 15ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በዓል በሚከበርበት ዙሪያ የበዓሉ አስተባባሪ ኮሚቴ በድሬዳዋ መወያየት ጀመረ። 

ወይይቱ ሲጀመር የተገኙት የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ 15ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል የሚከበረው በድሬዳዋ አስተዳደር መሆኑን ገልጸዋል።

በዓሉ የሚከበረው የኢትዮጵያዊያንን የርስ በርስ ግንኙነት በሚያጠናክርና ኢትዮጵያዊ እሴቶችን ጠብቆ ለማስቀጠል በሚያስችሉ ተግባራት መሆኑን ተናግረዋል።

ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለማዳበር በሚያስችሉ መሰናዶዎች በዓሉ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ እንደሚከበር አስታውቀዋል።

እንደ አፈ-ጉባኤ ገለጻ ቀደም ሲል የተከበሩበት በዓላት ያስገኙትን ጥቅሞች ከመጠበቅ በተጓዳኝ የነበሩ  ውስንነቶችን በሚያስተከክል  መንገድ ይከበራል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ በበኩላቸው ቀደም ሲል የተከበሩት  በዓላት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ማንነት በሚገባ እንዲታይና እንዲታወቅ እንዲሁም እሴቶቻቸውንና የርስ በርስ ግንኙነታቸውን ፍሬያማ እንዲሆን አግዘዋል ብለዋል፡፡

በመጪው ህዳር 29 በዓሉ በድሬዳዋ  መከበሩ የተለያዩ የልማት ተግባራት ለማከናወን የሚያግዝ ከመሆኑም በላይ  አንድነትን በማጠናከር ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ለማድረግ ጥሩ መደላደል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

በዓሉ የደመቀና ያማረ ለማድረግ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጸው ለዚህም የአስተዳደሩ ነዋሪዎች፣የፌደራል መንግስትና የተጎራባች ክልሎች የተለመደ ድጋፍ እንዲያደርጉም  ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኮሮና  ሁኔታ መተንበይ ስለማይቻል  በዓሉ በጋራ መከበር ባይቻል እንኳ ከወዲሁ ወረርሽኙ ታሳቢ ያደረገ አማራጭ መንገድ ሊቀየስ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ድሬዳዋ በተጀመረው መድረክ የአምናውን በዓል አከባበር ሪፖርት እና የ15ኛው በዓል መነሻ ዕቅድ ለተሳታፊዎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ነው፡፡

በውይይቱ የሁሉም ክልሎች እንዲሁም የአዲስ አበባና ድሬዳዋ አስተዳደሮች  ምክር ቤቶች አፈ-ጉባኤዎችና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም