ኮርፖሬሽኑ በተደረገው ማሻሻያ የስኳር ምርት እድገት ማሳየቱን ገለፀ

54

 አዲስ አበባ ነሀሴ 3/2012 (ኢዜአ) በመንግስት በተደረገው ማሻሻያ የስኳር ኢንዱስትሪ ትልቅ የምርት እድገት ማሳየቱን የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን አስታወቀ። 

የኮርፖሬሽኑ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጋሻው አይችሉህም ለኢዜአ እንዳሉት፤ ለውጡን ተከትሎ የስኳር ፕሮጀክቶች በመንግስት ቅድሚያ ተሰጥቷቸዋል።

''በስኳር ፕሮጀክቶች የተደረገው ማሻሻያ የሚበረታታና ውጤት ያስገኘ ነው'' ያሉት ኃላፊው፤ በተጠናቀቀው በጀት አመት ሶስት ሚሊዮን ኩንታል ስኳር መመረቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ባለፉት ሁለት አመታት ከፍተኛ ምርት ማምረት እንደተቻለ አስታውሰዋል።

ከስኳር ምርት በተጨማሪ የኢታኖል ምርትም ውጤት እንዳመጣ ተናግረዋል።

ፊንጫና መተሃራ ስኳር ፋብሪካዎች በአገሪቱ ያሉ ኢታኖል አምራቾች መሆናቸውን ተናግረው፤ በ2012 በጀት አመት 14 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሊትር ኢታኖል መመረቱንም አስረድተዋል።

''ይህም ከቀደመው በጀት አመት ጋር ሲነፃፃር የ6 ሚሊዮን ሊትር ብልጫ አሳይቷል'' ብለዋል።

በኢንዱስትሪው የአገር ውስጥ ባለሙያዎችን አቅም ማጎልበት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀው፤ የማሻሻያው አንዱ ውጤት ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎችን ጥገናዎችን በራሳቸው እንዲከውኑ ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።

በአገሪቱ የተካሄደውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ ተከትሎ መንግስት የስኳር ፋብሪካዎችን ወደግል ለማዛወር መወሰኑን አስታውሰው፤ ሂደቱ በኮቪድ-19 ሳቢያ መዘግየቱን አስረድተዋል።

ብድር ላለባቸው ፋብሪካዎች የፕራይቬታይዜሽን ሂደቱ ወሳኝ ከመሆኑ ባሻገር የኢንዱስትሪውን ቅልጥፍና እና ውጤታማነትን የሚያሻሽልና አገሪቱን በረጅም ጊዜ ስኳር ወደውጭ መላክ የሚያስችላት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ስድስት የስኳር ፕሮጀክቶች ወደግል ለማዘዋወር ሂደቱን ባጠናቀቀበት የፈረንጆቹ የዘመን ቀመር የ2020 የመጀመሪያው ሩብ አመት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም