የትምህርት መሠረተ ልማት ማነስ ተማሪዎችን ባሉበት ለማስተማር እንቅፋት ሆኗል

135

 አዲስ አበባ ነሀሴ 3/2012 (ኢዜአ)   የትምህርት መሠረተ ልማት   አነስተኛ መሆን በኮሮናቫይረስ የተቋረጠውን ትምህርት ለማካካስ በሚደረገው ጥረት ላይ ችግር መፍጠሩን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት ሳይቀንስ በ2013 ትምህርት የሚቀጥል ከሆነ የተማሪዎችን ጥግግት ለመቀነስ የተለያዩ ማህበራዊ ተቋማትን ጭምር ለማስተማሪያነት ለመጠቀም መታሰቡንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

የኮቪድ-19 ስርጭት በትምህርት ቤቶች እንዳይስፋፋና የመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ችግር እንዳይፈጠር መንግስት ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ማድረጉ ይታወሳል።


በእዚህም 26 ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነው በቤት ውስጥ እንዲቆዩ መደረጉን በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት መሠረተ ልማት መስፋፋት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ ለኢዜአ ገልጸዋል።


የተቋረጠውን የክፍል ውስጥ የገጽ ለገጽ ትምህርት ለማካካስ የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ተማሪዎች ባሉበት ሆነው እንዲከታተሉ የማድረግ ሥራዎች መጀመራቸውንም እንዲሁ።

ለእዚህም እንደ ትምህርት በሬዲዮ፣ የቴሌቪዝን ትምህርት፣ በማህበራዊ ድረ-ገጽ፣ ኦንላይንና መሰል የትምህርት መሠረተ ልማቶችን በመጠቀም ትምህርት እንዲሰጥ መደረጉን በማሳያነት አንስተዋል።

ይሁንና እነዚህ የትምህርት መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት በኩል እንደአገር ክፍተት መኖሩንና በታዳጊ ክልሎች ችግሩ የበለጠ የሰፋ መሆኑ በቴክኖሎጂ ተደግፎ በሚሰጠው ትምህርት ላይ እንቅፋት መፍጠሩን አቶ ሚሊዮን ተናግረዋል። 

በመንግስት በኩል ክፍተቱን ለማጥበብ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

እንደሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ጫና ለመቀነስ በአዲስ አበባ እና በአንዳንድ የክልል ከተሞች የትምህርት መሰረተ ልማቶችን በመጠቀም ትምህርት መስጠት ተጀምሮ ነበር።


ይሁንና በአገሪቱ ከ80 በመቶ በላይ ተማሪዎች የትምህርት መሠረተ ልማትና ቴክኖሎጂ ባልተሟሉባቸው አካባቢዎች መኖራቸው በማካካሻ የትምህርት አሰጣጡ ላይ ይበልጥ ተግዳሮት ማሳደሩን ገልጸዋል።

በቀጣይም የትምህርት ዘርፉን ሊፈታተኑ የሚችሉ ተመሳሳይ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተሰራ መሆኑን አቶ ሚሊዮን ተናግረዋል።

“በአሁኑ ወቅት የሚስተዋለውን የመሠረተ ልማቶች ክፍተት መሙላት የሚያስችል የ10 ዓመት የትምህርት ልማት ዕቅድ ተዘጋጅቷል” ብለዋል።

አቶ ሚሊዮን እንዳሉት በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ትምህርት ቤቶች ከተከፈቱ ሊፈጠር የሚችለውን ጫና ለመቋቋም ቀደም ሲል ትምህርት ቤቶቻቸውን ከከፈቱ አገራት ልምድና ተሞክሮ እየተወሰደ ነው። 

በእዚህም በአሁኑ ወቅት ትምህርት ቤቶቻቸውን ክፍት ያደረጉ አገራት በክፍል ውስጥ የተማሪ ቁጥርን በፊት ከነበረው በመቀነስ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።


በኢትዮጵያም የተማሪዎችን ጥግግት ለመቀነስ የተለያዩ ማህበራዊ ተቋማትን ጭምር ለመማር ማስተማሪያነት በጊዜያዊነት ለመጠቀም መታሰቡን ገልጸዋል።


የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለመግታት ሲባል 184 አገራት በወሰዱት ትምህርት ቤቶችን የመዝጋት እርምጃ በዓለም ላይ ወደ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

ከእነዚህ 184 አገራት ውስጥ እስካሁን ድረስ ትምህርት ቤቶቻቸውን የከፈቱት 83 ብቻ መሆናቸውም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም